የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል የ7ወር ሪፖርቱን አቀረበ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል የ2014 በጀት ዓመት የሰባት ወር የስልጠና አፈጻጸም ሪፖርቱን በአዳማ ከተማ ሮቢ ሆቴል ለግምገማ እና ውይይት አቀረበ፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የውይይት መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት የስልጠና ማዕከሉ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ በተመሰረተ ሁኔታ ወደ ስራ በመግባቱ አጥጋቢ የሆነ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንና እንዲህ አይነት የውይይት መድረኮች ደግሞ የሰራናቸውን መልካም ስራዎች ብቻ የምናነሳባቸው ብቻ ሳይሆኑ ያልሰራናቸውን ስራዎች በማስቀመጥ በመወያየት በቀጣይ የምንማርባቸውን መንገዶች የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ አህመድ የስልጠና ማዕከሉ ዳይሬክተር በመድረኩ ላይ የማዕከሉን አመሰራረት፣ ተልዕኮ፣ የማኔጅመንት ሂደት፣ የሚያተኩርባቸውን የስልጠና መስኮች፣ በአፈጻጸሙ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲሁም በአጠቃላይ የተከናወኑ ተግባራትን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ የስልጠና ማዕከሉ የኢንስቲትዩቱን አጠቃላይ የስልጠና ፕሮግራሞች ተቋማዊ በሆነ መልክ ለመምራት እንዲረዳ በ2009 ስራ የጀመረ ሲሆን ይህን ለማከናወን እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በዚህ በጀት ዓመት የስልጠና ፕሮግራሞችን ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ማዕከሉ ከሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል፣ ከምርምር እና የክልል ላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬቶች ጋር በጠበቀ ሁኔታ የተሳኩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
አቶ መሐመድ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለ9188 ለሚሆኑ ሰልጣኞች በተለያየ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ በሰባት ወራቱ ውስጥ ለ6961 ሰልጣኞች በተለያየ ዘርፍ ስልጠና እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በዚህም ከዓመቱ ዕቅድ 76 በመቶ ማሳካት ማቻሉን ያብራሩ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘም የስልጠና ሞዲውል ዝግጅት የተደረገ ሲሆን እስካሁን ማዕከሉ 20 የሚሆኑ ሞዱሎችን አዘጋጅቶ ከዚህ ውስጥ አስሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እውቅና ያገኙ ሲሆን ስምንቱ እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
“ስልጠናዎች የሚሰጡት እርግጥም ያሉ ክፍተቶችን በትክክል ለመሙላት የሚያስችሉ ናቸው ወይ የሚለው በመጀመሪያ የዳሰሳ ጥናት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ በኢንስቲትዩቱ ባደረግነው ጥናት በይበልጥ ከመጀመሪያ ሶስቱ ፍላጎቶች ውስጥ Statistical Software, Research Methodology እና Project Management and Leadership ላይ የመሰልጠን ፍላጎት እንዳለ መረዳት ችለናል፣” በማለት አቶ መሐመድ ያብራራሉ፡፡
በአጠቃላይ የስልጠናዎቹ ዓይነት 68 በመቶ መሰረታዊ፤ 21 በመቶ ደግሞ በተለያዩ ወርክሾፖች እና ስልጠናዎች የተሳተፉ ናቸው፡፡ ከሰልጣኞቹ 74 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ ስልጠና ከተሰጣቸው 50.3 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከድንገተኛ አደጋና ወረርሽኝ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስልጠናዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ ስልጠናዎችን ሙሉ በሙሉ በመመዝገብ ጠንካራ የሪጅስትራር ስርዓት የዘረጋ ሲሆን ወደፊትም የህን ሂደት ለማዘመን ከሌሎች ተቋሞች ጋርም እየሰራ ይገኛል።ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው በም/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቶሌራ እና የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ምላሽ ተሰጥቷል።