ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ ያሉ የኢኖቬሽን ስራዎችን ጎበኙ

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው ከኢንስቲትዩቱ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት እንደተናገሩት ላለፉት መቶ አመታት የህብረተሰብን ጤና በማሻሻል ረገድ በፈጸመው አኩሪ ተግባር በሀገራችንም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ መልካም ስም ያተረፈው ይህ ኢንስቲትዩት ታሪኩን እና አገልግሎቱን የሚመጥን አሰራር እና ዉበት እንዲኖረው ለማስቻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የሪፎርም ስራዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርበት እንደሚከታተል የተናገሩት ዶ/ር ደረጀ በምርምር፣ በላብራቶሪ አገልግሎት፣ በድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር፣ እንዲሁም በጤና መረጃ አስተዳደር ዙሪያ ቀልጣፋና የዘመነ አስራር እንዲኖር እየተገበረ ያለው የዲጂታላይዜሽን ስራዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው አያይዘውም ምድረ ጊቢውን እና የስራ ቦታዎችን ውብ፣ ምቹ እና ፅዱ ለማድረግ የተሰሩ እና በመሰራት ላይ ያሉ ስራዎች ለሰራተኞችም ሆነ አገልግሎት ፈልገው ወደ ኢንስቲትዩቱ ለሚመጡ ተገልጋዮች እርካታን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ኢንስቲትዩቱ ከበርካታ አለማቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት ስለሚስራ ለሀገር ገጽታ ግንባታም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱን በአፍሪካ በህብረተሰብ ጤና የልህቀት ማእከል ለማድረግ ውጥን ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው የዲጂታል ስራዎች እስከ ወረዳ ድረስ ተግባራዊ እየተደረጉ በመሆናቸውን የበሽታ ቅኝት፣ የድንገተኛ አደጋዎች የመሳሰሉ ስራዎች ላይ አጥጋቢ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን፤ የላብራቶሪ አገልግሎትንም በማስፋፋት በክልሎችም ያለዉን ተደራሽነት ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ እድሜ ጠገብ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ ከሚሰጣቸው በርካታ ዓይነት አገልግሎቶች፣ ካለው አለማቀፍ ግንኙነት እና የሰው ኃይል ብዛት አንጻር በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅ ገልፀው የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች እና አመራሮች በቁርጠኝነት በመስራታቸውም ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎችም የጤና ሚኒስቴር ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡