ሀገር አቀፉን የጤና ደህንነት መርሀ ግብር እቅድ ለማዘጋጀት የሚረዳ ስልጠና ተሰጠ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የተቀናጀ ገለልተኛ የጤና ደህንነት አቅም ግምገማ በማድረግ ብሎም የጤና ደህንነት መርሀ ግብር እቅድ ለማዘጋጀት በሂደት ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም በዚህ የስራ ሂደት ላይ ለሚሳተፉ ለሁሉም ሴክተሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ የአለም አቀፉ የጤና ደንብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አስተባባሪና የአንድ ጤና አስተባባሪ በዚሁ የአቅም ግንባታ ስልጠና መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገር አቀፉ የጤና ደህንነትን ለመተግበር ይቻል ዘንድ ሁሉም ሴክተሮች በአሁኑ ወቅት እያደረጉ ያሉትን በጋራና በተቀናጀ መለኩ ተናቦ በስራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ቀጣዩ ሀገር አቀፍ የጤና ደህንነት የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመቅረጽ ለማስፈጸም እና ለክትትል ስራዎች ጠቃሚ የሚሆኑ ግብአቶችን ለማሰባሰብ እንደሚረዳ ለማወቅ ተችልዋል፡፡
ይህ ስልጠና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን በስልጠናው ላይ ቁጥራቸው አርባ የሚሆን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአርመር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለስልጣን፣ ከአለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ጽ/ቤትና ከሪዞልቭ ቱ ሴፍ ላይፍ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆየው ይህ ስልጠና ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በመጡ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአለም የጤና ድርጅትና የሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭስ ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡