ሀገር አቀፉ የህብረተሰብ ጤና ጉባኤ ተካሄደ።

ሀገር አቀፉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንሲትቲዩት የ2015 በጀት አመት አንደኛው የህብረተስብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም በዛሬው እለት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ ተጀመረ፡፡
ክቡር አቶ ፀጋዬ ማሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ዋና ተጠሪና የዕለቱ የክብር እንግዳ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የክልሉ መንግስት በክልሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት፡ ቅድመ ዝግጅት እና ምላሽ አሰጣጥ እንዲጠናከር እና የክልሉን ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲደራጅ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የማህበረሰብ እና የሁኔታዎች የጤና ቅኝትን በተመለከተ በማህበረስብ ደረጃ እንዲወርድና እንዲጠናከር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ሚኒስቴር የቴክኒካል ተቋም በመሆን የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስራዎችን በማሳደግና በማጠናከር የተደራጀ ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የተዘረጋውን የህብረተስብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርአት በመጠቀም የተጠናከረ የቅኝት እና ምላሽ እንዲሁም መልሶ የማቋቋም ተግባራትን በመተግበር የማይበገርና ጠንካራ የጤና ስርአት ለመገንባት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ዘርፈ ብዙ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር የሕብረተስብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረሙ በሁለት ቀናት ቆይታው በሀገር አቀፉ የሕብረተስብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስራ ላይ የተከናወኑ ስራዎች የሚገመገግምበት፡ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሄ የሚፈለግበት፡ ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የሚቃኙበት እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በፎረሙ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከሰቱ የህብረተስብ ጤና አደጋዎች ላይ ውይይቶች የተካሄዱና በቀጣይ መከናወን ባለባቸው ርእሰ ጉዳየች ዙርያ ምክክር ተደርጓል፡፡ በፎረሙ ላይ ከጤና ሚኒስቴር፡ ከሁሉም ክልሎች የጤና ቢሮ እና የክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ ስብሰባው በነገው እለትም ቀጥሎ የሚውል ይሆናል።