ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት በአማራ ክልል በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከሌሎች ባድርሻ አካላት ጋር የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ጀመረ፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የፖሊዮ ማጥፋት ፕሮግራም ከተጀመረበት ከ1996 እኤአ ጀምሮ የፖሊዮ ማጥፊያ ስትራቴጂዎችን ማለትም የቅኝት ስራዎችን ማጠናከር፣ የመደበኛ ክትባት ሽፋንን ማሳደግ እና የክትባት ዘመቻዎችን የማካሄድ ስራዎች እንደቆዩ ይታወቃል።
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት ለነዚህ ስራዎች ላለፉት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራታቸዉ ምክንያት ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የዋይልድ ፖልዮ ቫይረስ ሪፖርት ያደረገችው በጥር ወር 2006 ዓ.ም በመሆኑ እና በ2009 ዓ.ም ከዋይልድ ፖሊዮ ነፃ መሆኗን በአፍሪካ ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳረጋገጠ እና በአሁኑ ሰዓት የዋይልድ ፖሊዮ በሽታ በአፍሪካ አህጉርም ለመጥፋቱ ማረጋገጫ የተሰጠ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በአጎራባች ሀገሮች ሲዘዋወር የቆየ በክትባት እጥረት የሚመጣዉ የፖሊዮ ቫይረስ ከታህሳስ/ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአጠቃላይ በአገራችን መኖሩ ከሰው እና ከአካባቢ ከተወሰዱ ናሙናዎች በተሰራ ቅኝት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ለዚህ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎችና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም ከሌሎች ባድርሻ አካላት ጋር በመሆን የህፃናትን የፖሊዮ በሽታ የመከላከል አቅምን በማሳደግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት፣ ብሎም የፖሊዮ በሽታን ለማጥፋት ህጻናትን ከመደበኛው የክትባት አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ዙሮች የክትባት ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
በዚህ በ 2014 ዓመትም ከጥቅምት 12 እስከ 15 ለተከታታይ 4 ቀናት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለአስራ ስድስት ሚሊዮን ሰባት መቶ አርባ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ (16,748,200) እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት የተሰጠ ሲሆን የሁለተኛውን ዙር ክትባት ዘመቻ ደግሞ ከሚያዚያ 7 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚሰጥ ይሆናል፡፡
አቶ አስቻለው አያይዘውም ይህ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የበሽታውን ስርጭት በማስቆም በፖሊዮ ቫይረስ ምክንያት የሚከሰትን የልጅነት ልምሻና ሞትን ከሀገራችን ብሎም ከአህጉራችን አፍሪካ የማጥፋት ግብን ለማሳካት ታልሞ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ የማሕበረሰብ መሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች አንድም ሕጻን ይህ ክትባት እንዳያመልጠው የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በማለት ተናግረዋል፡፡