ለላቦራቶሪ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
የኢንስቲትዩቱ የባክቴሪያል፣ፓራሳይቲክ እና የእንሰሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና
ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የላቦራቶሪ ምርመራን ወጤታማ በማድረግ ወባን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት
ከሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች ከነሃሴ 10 እስከ 14/2011 ዓ.ም የአቅም
ግንባታ ስልጠና ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ የወባ በሽታ በላቦራቶሪ በጥራት ተመርምሮ ትክክለኛ መድሃኒት እንዲያገኝ
በማድረግ የሚሰጠው የህብረተሰብ ጤና አገልግሎትን በማሻሻል ተአማኒነትን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ
ስልጠና ነው፡፡
ዶ/ር አዱኛ ወዬሳ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ የስልጠናውን የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት
እንደገለጹት የማይክሮስኮፒክ የምርመራ ዘዴን በማሻሻል በኩል በትክክል አገልግሎቱን መጠቀም
እንዲቻልና ክፍተቶችን በመለየት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወባን የማስወገድ ስራን በሃገር ደረጃ
ለመስራት ትልቅ መሰረት የሚጣልበት ስልጠና መሆኑንና በጤና ሚኒስቴርና በአጋር ድረጅቶችም ከፍተኛ
ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለ ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማይክሮስኮፒክ የምርመራ ዘዴ አሁን ባለው ሁኔታ ሲታይ ተመሳሳይ የእውቀት ደረጃ ላይ አይደለንም
በመሆኑም ይህ ስልጠና ወደ ተመሳሳይ የእውቀት ደረጃ በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው ሲሉ
ዶ/ር አዱኛ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አቶ መብራሃቶም ኃይለ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ በበኩላቸው የወባ በሽታ በሃገራችን ሰፊ
የህብረተሰብ የጤና ችግር ነው፤ አሁንም ከጥንት ጀምሮ የወባ ስርጭት በሚታይባቸው ቦታዎች ከፍተኛ
ሆኖ ይገኛል፡፡በመሆኑም ይህ ስልጠና የጤና ሚኒስቴር ዋና ፕሮግራም ሲሆን የላቡራቶሪ ባለሙያዎች
ወባን ከመመርመር አንጻር የሚታየውን የእውቀት ውሱንነት በመቅረፍ የወባ በሽታን በተሸለ ደረጃ
ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ታስቦ የተዘጋጀ ስለጠና ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከስልጠናው በኋላ ባለሙያዎች ወባን በመመርመር ስራ ላይ በየጤና ተቋማት የሚገኙ የላቡራቶሪ
ባለሙያዎችን ችግራቸውን እና ያሉባቸውን የእውቀት ክፍተቶች በመለየት የማስልጠንና ወባን በላቡራቶሪ
መመርመር እውቀታቸውን መገንባትና ድጋፍ የመስጠት ስራን በትኩረት እንደሚሰሩ ስልጠናውን
ሲያስተባብሩ ከነበሩት ከኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታ መቆጣጠርን ማስተባባር ላይ ከሚሰሩት
ከአቶ በኩረ-ጽዮን ግደይ መረዳት ተችሏል፡፡
በማይክሮስኮፒክ ወባን የመመርመር ዘዴን እንዲሁም የመረጃ አያይዝንና ግብአትን አስመልክቶ ካሉ
ችግሮች በመነሳት መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ በገለጻና በተግባር ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
የረጅም ጊዜ ልምድ፣ ከስልጠና በኋላ ባለሙያዎችን የማስልጠን እና የማብቃት ልምድ ያላቸው
እንዲሁም እየሰሩ ማሰልጠን የሚችሉ 26 የላቡራቶሪ ባለሙያዎች በስልጠናው ላይ ተሳትፈዋል፡፡