ለባሕል መድሐኒት ማደግ በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተገለጸ
November 15, 2019
የኢንስቲትዩቱ ባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት የባህል ህክምና ፍኖተ ካርታ አፈጻጸም ስልት እና በትስስር ተባብሮ የመስራት አቅጣጫ ለመቀየስ ያዘጋጀው የምክክር ግምገማዊ ዎርክሾፕ በአዳማ ከተማ ከህዳር 2-3/2012 ተካሄደ፡፡
ወርክሾፑ ለአስር ዓመቱ የጤና እቅድ፣ ለጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ-2፣ ለብሔራዊ የመድሐኒት ማምረትና ማጎልበቻ ዕቅድ፣ ለምርምር ተቋሞች ስትራቴጂክ ዕቅዶች፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ጠቃሚ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ የታለመ እንደሆነ የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶ/ር አስፋው ደበላ በመክፈቻው ዕለት አስረድተዋል፡፡
ወ/ሮ ፍሬህይወት ተካ የባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የባህል መድሐኒት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው እና በጤና ስርዓቱ ውስጥ እንደሚካተት እና ከዎርክሾፑም ለጤናው ዘርፍ የቀጣይ 10 ዓመት ዕቅድ ግብዓት እንደሚጠበቅ በመግለጽ ዎርክሾፑን አስጀምረዋል፡፡
በዎርክሾፑ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ባሕላዊ መድሐኒት አዋቂዎች ባጠቃላይ ከ50 በላይ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የቡድን ውይይት አድርገው የውይይታቸውን ውጤት በማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡