ለተፈናቀሉ ወገኖች የእርዳታ ድጋፍ ተደረገ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በጦርነቱ የተነሳ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰቡትን ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች የማስረከብ መርሀ ግብር አከናወኑ፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር የተቋሙ ሠራተኛ ከዚህ በፊትም የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ መሆኑን አውስተው ቀደም ሲል ሠራተኛው ከሰጠው የአንድ ወር ደመወዙ በተጨማሪ ከሠራተኞች የተገኘው የገንዘብ የአልባሳትና ልዩ ልዩ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች በጦርነቱ የተነሳ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ይህ እርዳታ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አስገንዝበው በተቋሙ ስም መርሀ ግብሩ እንዲሳካ ያስተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
በዚሁ መርሀ ግብር ላይ እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት 35 የተቋሙ ሠራተኞች ወደ ግንባር በመዝመት የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ግዴታ ለመወጣት ፍቃደኛ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የደም ልገሳ መርሀ ግብርም 55 የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች ደም የለገሱ ሲሆን ቀጣዩም መረሀ ግብር በቅርቡ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በመርሀ ግብሩ ላይ የሠራተኞች ተወካይ እንዲሁም የመርሀ ግብሩ አስተባባሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡