ለኤች አይ ቪ ህሙማን የሚሆን አዲስ የቲቢ መመርመሪያ ዘዴ ሊተገበር ነው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኤች አይ ቪ ህሙማን የሚሆን አዲስ የቲቢ መመርመሪያ ዘዴ የሽንት ናሙናን መጠቀምያን የሁሉም ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከክልል ላቦራቶሪዎችና የተለያዩ አጋር አካላት በተገኙበት ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም የማስጀመሪያ መርሀ ግብርን አካሄደ፡፡
በእዚሁ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር መክፈቻ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ ባደረጉት ንግግር የኤች አይ ቪ ህሙማን በሽታው በሚፈጥረው የሰውነት የመከላከል አቅም ማነስ ምክንያት የተለመደው የቲቢ አክታ ናሙና ለመስጠት እንደሚቸገሩ አውስተው በዚህም ምክንያት ከእነዚህ ታካሚዎች የሚገኘው ናሙና የቲቢ በሽታ የማመላከት ችግር እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ናሙናው ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ብዙ ግዜ የቲቢ በሽታን በኤች አይ ቪ ህሙማን ላይ ለመመርመር አዳጋች አድርጎት የቆየ በመሆኑ በእዚህም ምክንያት ቀላል የማይባሉ የኤች አይ ቪ ህሙማን ባልተመረመረ የቲቢ በሽታ ምክንያት እንደሚሞቱ አብራርተዋል፡፡ ስለዚህ የቲቢ በሽታን በኤች አይ ቪ ታካሚዎች ላይ የመመርመርን አቅም ለማሳደግ ከተለመደው የቲቢ መመርመሪያዎችና ናሙናዎች ውጪ ለኤች አይ ቪ ታማሚዎች የሚሆኑ የቲቢ ምርመራ ዘዴዎችን ካሉት ምርመራዎች በተጓዳኝ ማቅረብ አስፈላጊነቱ ታምኖበታል ብለዋል፡፡
ከእነዚህም አማራጮች አንዱ በሽንት ላይ የሚደረግ የቲቢ ምርመራ ኤች አይ ቪ በደማችው ውስጥ ለሚገኝ (Urine TB LAM test for PLHIV) ዘዴ ዋነኛው ነው ተብሏል፡፡ ይህ ምርመራ በተለይም የኤች አይ ቪ ህመም ለጠናባቸው እና የሲዲ ፎር መጠናችው ዝቅ ላሉ (Low CD4 , advanced HIV disease) ታካሚዎች የቲቢን የመመርመር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡
ስለሆነም በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሠረት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስተተዩት እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመመተባበር ይህንን ምርመራ በየኤች አይ ቪ ህክምና መከታተያ ተቋማት (ART treatment centers) ለመተግበር መዘጋጀታቸውን የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ተወካይዋ ወ/ሮ ምርቴ ጌታቸው በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በሃገራችን ከፍተኛ የጤና ችግር ከሚያመጡ በሽታዎች ውስጥም የቲቢ በሽታ አንዱ በመሆኑ የቲቢን በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ልዪ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የቲቢና ኤች አይ ቪ የምርመራ እና የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማትን በከፍተኛ ደረጃ የማስፋፋት ስራዎች፣ አዳዲስ የቲቢና መድሀኒት የተላመደ ቲቢ መመርመሪያ መሳሪያዎች (Gene x-pert) ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት አገልግሎቱን ተደራሽ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን የማህበረሰብ አቀፍ የቲቢ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ትግበራ የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ይህ የማስጀመሪያ መርሀ ግብርን የ TB-LAM መመርመርያን በመጠቀም የኤች አይ ቪ በሽታ ያለባቸዉ ህሙማን የቲቢ ልየታና ምርመራ ላይ በተጠናከረ መንገድ በመተግበርና የተገኘባቸዉን ሰዎች በአግባቡ በማከም የቲቢ በሽታ ስርጭትን በመቀነስ እና በመቆጣጠር በዓለማቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ስራ ላይ ከፍተኛ አስተዋፃኦ እንደሚያደርግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ በበኩላቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የመረሀ ግብሩ መጀመር በሚቀጥሉ ጊዚያት ያለውን የቲቢ ፕሮግራም አፈጻጸምን ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በማጠናከርና እንዲሁም በእዚህ መመሪያ የተቀመጡትን ዝርዝር ተግባራቶች እንዲከናወኑ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የቲቢ ልየታ፣ ምርመራና ህክምና የሚጀምሩ ሰዎች ቁጥር በሁሉም ክልሎች እንዲጨምር ማድረግ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የመርሀ ግብሩ ኮንፍስረንስ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሙያዊ ምክክሮችን እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡