ለዳሰሳ ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች እና አስተባባሪዎች ስልጠና መስጠት ተጀመረ
የኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ-ጤና እና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባባር አገር አቀፍ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነት ያለበትን ሁኔታ ለማወቅና ለመገምገም ለሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎች እና አስተባባሪዎች ከመስከረም 9 እስከ 15/2015 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትን በጤና ግብዓት፣ በአገልግሎት አጠቃቀም እና ውጤት በኢትዮጵያ የጤና ስርዓትን ማጥናት ነው፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በስልጠናው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የሚካሄደው አገር አቀፍ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽት ጥናት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሲሆን በዚህ ጥናት በከተማም ይሁን በገጠር ፍትሃዊና ጥራት ያለው የጤና ተደራሽነት እንዲሁም በጤናው አገልግሎት ዙሪያ ጉድለት ያለበትን ሁሉ የመለየት ስራ የሚሰራበት ጥናት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ እጅግ አስፍላጊ እና የህብረተሰቡን የጤና ችግር ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ በመረጃ ሰብሳቢዎቹ በኩል እጅግ ኃላፊነትን፣ተጠያቂነትን እና ሙሉ ጊዜን በመውሰድ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ባለሙያዎቹንም በታሪክ አጋጣሚ የዚህ ጥናት ተሳታፊ በመሆናቸው ደስ ሊላቸው እንደሚገባ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ስለሺ ጋሩማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ በበኩላቸው በእድሜ፣ በጾታ፣በሃብት፣በትምህርት እና ልዩ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔዎችን ለመወሰን ይቻል ዘንድ ይህ የተዘጋጀው አገር አቀፍ ጥናት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አረጋ ዘሩ በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ባለሙያ እና የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ባቀረቡት የጽሁፍ ገለጻ በዓለም ጤና ድርጅት ትርጉም መሰረት ፍትሃዊ የጤና ተደራሽት ማለት በተለያዩ ሰዎች፣ በማህበረሰብ መካከል ሊወገድ የሚችል ልዩነት ሳይኖር (ምንም እንኳን የማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብት፣ የዲሞግራፊ እና የጂኦግራፊ አኗኗር ልዩነት ቢኖርም) ጤና ለሁሉም ማህበረሰብ በፍትሃዊነት እኩል ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ አጠቃላይ ጥናቱ ምን እንደሚመስል እንዲሁም የመረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎችን ኃላፊነትና ግዴታ፣ የክትትል ስርዓትን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮዎች የተውጣጡ 100 መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ለ7 ቀናት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ማህብረሰቡን መሰረት ያደረገ በቆጠራ ቦታ የቤት ለቤት የዳሰሳ ጥናት መሰረት በማድረግ ፍትሃዊ የጤና ግብዓት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚነት እና ውጤት ተደራሽነት መረጃ የመሰብሰብ ስራ እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡