ለጤናው ሥርዓት መጠናከር መረጃ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገለጸ
ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የጤናውን ሴክተር ለማጠናከር ብሎም የተሻለ የጤና ሥርዓት ለመገንባት እና የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ “መረጃ ለተሻለ ጤና” በሚል ርዕስ በተከናወነው ኮንፍረንስ ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንዳስገነዘቡት መረጃ ለጤናው ሥርዓት ያለው ሚና እጅግ ቁልፍና መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ መረጃን መሰረት ያደረገ የጤና ስርዓት ለመገንባት እንዲቻል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ሊያ አያይዘውም የሚኒስቴር መ/ቤቱ ለመረጃ የሚሰጠው ትኩረት እንዲጠናከር፤ የመረጃ ባህል አጠቃቀም እንዲጎለብት፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጤና ስርዓቱን ለማዘመን እንዲቻልና የመረጃ (ዳታ) ጉዳይ የሁሉም አካላት ጉዳይ እንዲሆን ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንደሚሰራበት አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ ሚናውን ከፍ በማድረግ መረጃ ለህብረተሰቡ ጤና መሻሻል ተገቢውን ሚና መጫወት እንዲችል ለማድረግና የመረጃ ስርዓቱን እንዲዘምን ብሎም ሌሎች በርካታ ተያያዥ ስራዎች በኢንስቲትዩቱ የብሄራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማእከሉ በኩል እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፋዊ፤ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፋዊ ለውጥን ግንዛቤ ውስጥ ባስገባና የመጪውን የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎቶች ሊመልስ በሚችል መልኩ መዋቅሩን እየፈተሸና እያስተካከለ ተግባርና ሃላፊቱን በውጤታማነት ለመፈጸም ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አለምነሽ ሀይለማርያም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሄራዊ ጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማእከል አስተባባሪ በበኩላቸው ስለ ማእከሉ ዋና ዋና ስራዎች እና ክንውኖች ገለጻ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር አወቀ ምስጋናው የማዕከሉ አማካሪ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ለጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ በእለቱ በቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይቶች የተከናወኑ ሲሆን በኮንፍረንሱ ላይ ከሁሉም ክልሎች ጥሪ የተደረገላቸው የሙያው ባለሙያዎች ተካፋይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡