መለስተኛ የስነ-ሕዝብ እና ጤና አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ዋና ዋና ጠቋሚ መረጃዎች ይፋ ተደረጉ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እና የተሻለ የጤና አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመቀየስ የሚያስችል መለስተኛ የስነ-ሕዝብ የጤና ዳሰሳ ጥናት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ3ወራት ሲያካሄድ ቆይቶ ዋና ዋና የጥናቱ ጠቋሚ መረጃዎችን በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ አጋር ድርጅቶች ነሀሴ 21/2011 ዓ.ም በኢሊሊ ሆቴል ይፋ አደረገ፡፡
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት የተካሄደው የመለስተኛ የስነ-ህዝብ የዳሰሳ ጥናት ከሌሎቹ መሰል ጥናቶች የተለየ የሚያደርገው በጤና ተቋማት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸሻለ የመጣውን የጤና አገልግሎት በንጽጽር ከማሳየቱም በላይ ለተአማኒነቱም አለም አቀፍ መስፈርቶችን ተከትሎ የተሰራ በመሆኑ የተሻለ መረጃና ውጤት በማሳየት ለቀጣይ እንድንዘጋጅ የሚያድርግ የጥናት ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር አሚር አማን ኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ምንስትር የመክፈቻ ንግግር በደረጉበት ወቅት ዳሰሳ ጥናቱን አስመልክቶ እንደገለጹት በዚህ የዳሰሳ ጥናት ውጤት በርካታ ጥሩ ወጤቶች የታዩ ሲሆን በሁሉም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል የተመዘገበ ቢሆንም የህጻናት ክትባት፣ የወሊድ አገልግሎት እንክብካቤ እና መሰል የጤና አገልግሎት ላይ በሃገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሰጥተን በቀጣይ መስራት እንደሚገባን ጥናቱ በሚገባ አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በአገር-አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 305 የቆጠራ ጣቢያዎች የተካሄደ ሲሆን በ8,663 አባወራዎች ቤት እድሚያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ማለትም በመዉለድ የዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ 8,885 ሴቶች ላይ የጥናቱን መረጃ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ለክትባት መረጃ ዕድሚያቸው ከ2 እስከ 3 ዓመት የሆናቸው 1,028 ህጻናት እንዲሁም ለቁመትና ክብደት ልኬት ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 4,990 ልጆች በጥናቱ ተካተዋል፡፡
ይህ መለስተኛ የስነ-ሕዝብ እና የጤና ዳሰሳ ጥናት በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና
በኢትዮጵያ የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩትና በተለያዩ የጤና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተካሄደ ሲሆን የዓለም ባንክ ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ዩኒሴፍ ቴክኒክና የበጀት ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት የተካሄደውን የስነ-ሕዝብ የጤና ዳሰሳ ጥናት ከታች በሰንጠረዥ በዝርዝር እንደቀረበው የስ-ሕዝብ ጤና የዳሰሳ ጥናት ውጤት በንጽጽር ሲታይ በጤናው ዘርፍ ያለው የጤና አገልግሎት እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን በተለይም በ2011 ዓ.ም ወይም እ.ኤ.አ በ2019 የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ቀደም ሲሉ ከተካሄዱት መሰል ጥናቶች በከፈተኛ ልዩነት የጤናው አገልግሎት እየተሸሻለ መምጣቱን ማወቅ ተችሏል፡፡