መሠረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ተባለ፡፡
መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንዳስገነዘቡት መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ በተለይ ድንገተኛ የህብረተሰብ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ለተፈናቃይ ወገኖች መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለማቅረብ ከማስቻሉም በላይ የእያንዳንዱን ዜጋ ጤንነትና ደህንነት ከመታደግ አንጻር የሚኖረው ሚና እጅግ የላቀ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር መሰረት ዘላለም በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የህጻናት ዳይሬክተር በበኩላቸው የእናቶችና የህጻናት ሞት ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም ግን መሰረታዊ የሆኑ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ያላገኙ በርካታ ወገኖች በመኖራቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ እስትራቴጂዎችን በመቀየስ የጤና አገልግሎቶቹ ተደራሽነት ላይ በመስራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሚስስ ሳራ ማሳላ በኢትዮጵያ የዩኤንኤፍፒኤ ምክትል ተወካይ በበኩላቸው በመሰረታዊ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ዙርያ የተዘጋጀው ስልጠና በተለይ ሴቶችና ወጣት ልጃገረዶች ማተኮሩ ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሥነ-ተዋልዶ ጉዳዮች ትኩረት ከተነፈጋቸው ለበርካቶች ሞት መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ ይህ ስልጠና ለባለሙያዎች እንዲሰጥ መደረጉ አገልግሎቱን በማስፋፋቱ በኩል ትልቅ እገዛ እንደሚደርግ ጠቁመዋል፡፡
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ ከጤና ሚኒስቴር፤ ከዩኤንኤፍፒኤ እና ከአጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡