መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች ተውጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ጥቅምት 8/2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር በሰልጣኞች የምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደተናገሩት መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ለሁሉም ክልሎች በተለያየ ጊዜ የተሰጠ መሆኑንና ስልጠናውን የወሰዱ ባለሙያች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ወቅቱ በሚጠይቀው የመረጃ ልውውጥ መሰረት የተለያዩ በሽታዎችን ቀድሞ በመለየት በፍጥነት ሪፖርት በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ያስመዘገቡ መሆናቸውን፣ ለዚህም በብሄራዊ ደረጃ ያሉ መረጃዎች ቀልጣፋ መሆናቸው የነዚህ ውጤት ማረጋገጫ ከመሆኑም በላይ የስልጠናው ውጤታማነት በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አቶ ጃፈር ከዛሊ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር መዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ስልጠናው በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ የ Surveillance data በመጠቀም ወረርሺኝ በአንድ አካባቢ ቢከሰት ቶሎ በመለየት ሪፖርት የማድረግ ምላሽ የመስጠትና የመከላከል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በሶስት ዙር በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን ያገኙ የጤና ባለሙያዎች ስልጠናውን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን ያገኙት ስልጠና ሕብረተሰቡን ከጤና አደጋዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያረግላቸው ገልፀዋል፡፡
ሶስተኛውን ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ 29 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡በቀጣይም ተደራሽነቱን ለማስፋት ስልጠናውን ባላገኙ ቦታዎች በቀጣይነት እንደሚሰጥ ከመድረኩ መረዳት ተችሏል፡፡