መሠረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በአማራ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች ተወጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ለ3ኛ ጊዜ ሰኔ 3/2013 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በሰልጣኞች የምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት የስልጠናው ዋና አላማ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዊችን ለመከላከል፣ለመቆጣጠርና ምልሽ ለመስጠት የሚያስችል የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ማህበረሰቡ በተለያዩ የጤና አደጋ ወረርሽኞች አንዳይጋለጡ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በዚህ አስቸጋሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የጤና ባለሙያዎቹ ስልጠናውን አጠናቀው መመረቅ መቻላቸው ለተመራቂዎቹም ለሕብረተሰቡም ትልቅ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ባለሙያዎቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ እና ስልጠናውን ላላገኙ ባለሙያዎች በማካፈል እንዲሁም ድጋፍ በማድረግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ጃፈር ከዛሊ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር መዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ስልጠናው በሶስት ዙር መሰጠቱን የገለጹ ሲሆን መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ የበሽታ ቅኝት መረጃ አሰባሰብ፣ የቅኝት ጥቅል ሪፖርት ምንነትና ምሉዕነት፣ መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች፣ በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶች፣ ወረርሺኝ በአንድ አካባቢ ቢከሰት ቶሎ በመለየት ሪፖርት የማድረግና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ አበረ ሙጬ የክልሉ የስልጠና አስተባባሪ በበኩላቸው እስካሁን መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ከተሰማሩት ባለሙያዎች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆኑንና መረጃዎችን በተገቢው መንገድ በመያዝና ለሚመለከተው አካል ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በመስጠት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ በላይ በዛብህ የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣አቶ አብርሃም አምሳሉ የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ የአፍሪካ ፊልድ ኢፕዲሞሎጂ ኔትወርክ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ዳይሬክተር በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት ስልጠናውን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ስልጠናውን ያገኙ የጤና ባለሙያዎች ስልጠናውን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን ያገኙት ስልጠና ሕብረተሰቡን ከጤና አደጋዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴ ሁሉ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሶስተኛውን ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ 32 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት የተሰጣቸው ሲሆን በአጠቃላይ ስልጠናው መሰጠት ከጀመረበት እስካሁን 134 የጤና ባለሙያዎች በስልጠናው የተሳተፉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 119 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ባለሙያዎች መመረቃቸውን እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጅ ከታቀደው የስልጠና ሽፋን አንጻር በአማካይ 60 ፕርሰንት የደረሰ ከመሆኑም በላይ ይህንንም ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ተደራሽነቱን ለማስፋት ስልጠናውን ባላገኙ ቦታዎች በቀጣይነት እንደሚሰጥ ከመድረኩ መረዳት ተችሏል፡፡