መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ለአጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ስርተፍኬት ተሰጣቸው፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ከተለያዩ ወረዳዎች ተውጣጥተው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ለ3 ወራት ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ጥቅምት 1/2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው 3ኛው ዙር ማጠቃለያ ስልጠና ላይ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ በሽታዎችና ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና ለጤና ባለሙያዎች በመስጠትና አቅም በመገንባት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታስቦ የሚሰጥ ስልጠና ነው፡፡
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስልጠናውን አስመልክቶ እንደተናገሩት በአገር አቀፍ ደረጃ እተሰጠ የሚገኘው የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በወረዳ ደረጃ ያለውን ኢፒዲሞሎጂ አቅም ማሳደግ ሲሆን አሁን የተሰጠው ስልጠና ከነበሩት ስልጠናዎች ሁሉ የሚለየው በ CPD እስታንዳርድ የእውቅና ስርተፍኬት የተዘጋጀለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም ወ/ሮ ነኢማ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የሚከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኞችን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የምላሽ ስራዎችን አጠንክረው በመስራት ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ መሐመድ አህመድ የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር በስልጠና ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል የጤና ባለሙያዎችን በእውቀት አቅም ለማጎልበት ተቋማዊ ይዘት ያለውን ስርዓት በመዘርጋት፣ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እና በሞጁል የተደገፈ ስልጠና በመስጠት አለም አቀፍና አገር አቀፍ የጤና አደጋ ወረርሽኞችን በመከላከልና በመቆጣጠር በርካታ ስራዎች ተስርተዋል ብለዎል፡፡
እየተሰጠ የነበረው ስልጠና ከሌሎች ስልጠናዎች በተለየ መልኩ ለ3 ወራት ተከታታይነት ያለው ከመሆኑም በላይ የጤና ባለሙያውን የሞያ ፈቃድ ለማደስ እንደቅድመ ሆኔታ ተደርጎ የሚታይ Continuous Professional Development (CPD) ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ ለባለሙያዎቹ የተሰጠ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ተወካይ በበኩላቸው ስልጠናውን አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡
ሰልጣኝ ባለሙያዎች በስራ ቦታ የተሰጧቸውን የፊልድ ፕሮጀክት አጠናቀው በጽሁፍና በፊት ለፊት ገለጻ አቅርበው የተመዘኑ ሲሆን አጠቃላይ የተሰጣቸው ስልጠና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የእለት ከእለት የጤና አገልግሎቶች ውጤታማ እና በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ እውቀት እንዳስጨበጣቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ ስልጠናውን ተከታትለው እና ተሳትፈው ያጠናቀቁ አማካይ ውጤታቸው 70 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ 31 የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡