መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጣቸው
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በአማራ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች ተወጣጥተው በሶስት ዙር መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጣና ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ በሶሊያና ሆቴል የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዊችን ለመከላከል፣ለመቆጣጥርና ምልሽ ለመስጠት የሚያስችል የጤና ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ማህበረሰቡ በተለያዩ የጤና አደጋ ወረርሽኞች አንዳይጋለጥ ማድረግ ነው፡፡
አቶ ጃፋር ከዛሊ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር መዕከል የዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ እንድገለጹት ስልጠናው በሶስት ዙር መሰጠቱን ገልጸው፤ በመጀመሪው ዙር መሰረታዊ የኮምፒውተር እወቀት፣ የበሽታ ቅኝት መረጃ እንዴት እንደሚሰበሰብ፣የቅኝት ጥቅል ሪፖርት አደራረግ እና የሚቀርቡ ሪፖርቶች ምሉዕነት ማካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች እና በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት ስራ ስርተው ለሁለተኛ ዙር ስልጠና እንዲመጡ የሚያስችላቸውን ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር ስልጠና ደግሞ ገለጻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዴት ይቀርባል፣ ወረርሺኝ በአንድ አካባቢ ቢከሰት በቅድሚያ ምን መደረግ አለበት፣የወረርሺኝ ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በምን መልኩ ይቀርባል፣ምን ምን ጉዳዮች ማካተት አለባቸው፣ የወረርሽኙስ መንስኤ ምን ነበር፣ የትኛው የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃ የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን አስተባባሪው አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞች የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስዶ የተሰራ ሪፖርት እና በሁለተኛ ዙር ስልጠና ወቅት የተሰጣቸውን የቅኝት ስራ እንዲያቀርቡ መደረጋቸውን፣በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር ስልጠና 48 ፣በሁለተኛው ዙር ስልጠና 41፣በሶስተኛው ዙር የመስክ ስራ የውጤት ምዘና ወቅት 41 ባለሙያዎች የተሳተፉ መሆናቸውን፣ በአጠቃላይ በሶስቱም ዙር ስልጠናና ምዘና ተሳትፈው ያጠናቀቁ አማካይ ውጤታቸው 70 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ 32 የጤና ባለሙያዎች የእውቀና ስርተፍኬት የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ጃፋር ከዛሊ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
አቶ አሌይ አያል የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደተናገሩት አሁን ባለው ሁኔታ የተለያዩ ወረርሽኛች እየተከሰቱ ባሉበት ሁኔታ እነዚህን የመሳሰሉ ስልጠናዎች ለባለሙያዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡በመሆኑም እናንተ ያገኛችሁትን እውቀት ይህንን የስልጠና እድል ላላገኙ ባለሙያዎች ልታካፍሉና ልታግዙ ይገባል፤ምክንያቱም በቀጣይ ሊሰጡ ለሚታሰቡ ስልጠናዎች የሚወሰኑት በእናንተ ተግባራዊነት ላይ ይሆናል፡፡ስለዚህ ያገኛችሁትን የአቅም ማጎልበቻ እውቀት ወደ ተግባር እንድትለውጡት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከመጀመሪው ዙር እስከ መጨረሻው ዙር የተሰጠው ስልጠና ከምንሰራው መደበኛ ስራ ጋር ብቻ ሳይሆን እለት ከእለት ከምንሰራቸው የግል ህይዎታችንም ጭምር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጠንና ወገናችንን የምናግዝበት የእውቀ ስልጠና ነበር ሲሉ ሰልጣኞች የስልጠናውን ጠቀሜታ በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡