መቀንጨርን ለመቀነስ ሲተገበር የቆየው ፕሮግራም የተደራሽነት ጥናት ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ ምግብ ምርምር ዳይሬክቶሬት በጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር ቅንጅት እ.ኢ.አ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የቆየው የህጻናትን መቀንጨር የመቀነስ ፕሮግራም ተደራሽነቱን አስመልክቶ የተሰራ ጥናት በመጠናቀቁ ግንቦት 6/2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ለባለድርሻ አካላት ይፋ አደረገ፡፡
የጥናቱ ዋና አላማ የፕሮግራሙ ተደራሽነት ምን እንደሚመስልና የተገኘውን ውጤት ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ ነው፡፡ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ከጥናትና ምርምር፣ ከሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች እንዲሁም ከላቦራቶሪ አቅም ግንባታ አንጻር ኢንስቲትዩቱ እየሰራ የሚገኘውን በርካታ ስራዎች የገለጹ ሲሆን በጥናቱ ዘርፍ ከተሰሩት ስራዎች ውስጥ አሁን ይፋ እየተደረገ የሚገኘው የህጻናትን መቀንጨር ለመቀነስ የተሰራውን ፕሮግራም ተደራሽነት ምን እንደሚመስል የሚፈትሽ ዳሰሳዊ ጥናት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ የተካሄደው በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በአጠቃላይ 31 ወረዳዎች ሲሆን የህጻናትን የመቀንጨር ችግር ለመቀነስ ተግባራዊ የካሄደው ፕሮግራም በአተገባባሩ እና በተደራሽነቱ ላይ ትኩረት በማድረግ የተካሄደ ጥናት መሆኑን ከጥናቱ ጽሁፍ መረዳት ተችሏል፡፡
መቀጨርን ከመቀነስ አንጻር ከፕሮግራሙ የሚጠበቁ በርካታ መለኪያዎች መሻሻላቸው ተገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው በጥናቱ ከመመላከቱም በላይ ፕሮግራሙ ቀጣይነት እንዲኖረው በመንግስት ሊደገፍ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡
በቀረበው ጥናት ላይ ሰፊ ውይይት እና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የተጠናቀቀ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮ፣ የግብርና ቢሮ፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች እና የአጋር ድርጅት ተወካዮች በአውደ ጥናቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡