ምግብን ከባዕድ ነገር መቀላቀል ይቁም በሚል መሪ ቃል የዓለም የምግብ ቀን ተከበረ
ኢንስቲትዩቱ በዓለም ለ3ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ2ኛ ጊዜ “ዛሬ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለነገ ጤና” “safe food now for a healthy tomorrow” በሚል መሪ ቃል የዓለም የምግብ ቀን በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የመስብሰብያ እዳራሽ አከበረ።
በዕለቱም የኢንስቲትዩቱ የምግብ ሳይንስ እና የስነ-ምግብ ምርምር ዳሬክተር ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በጤና እና በምግብ ዘርፍ ከፍተኛ የአሰራር ለውጥ እንዳለ ጠቁመው፣ በምግብ ደህንነት ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ፣ ከ40% በላይ ህፃናት በምግብ ደህንነት እንደሚጠቁ፣ የምግብ ደህንነት በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ እንዲሁም ከመቀንጨር ጋር በተያያዘ ህጻናት ለከፍተኛ ችግር እንደሚጋለጡ ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም ህጋዊ ያልሆነ የግብይት ስራ በዋናነት በኢትዮጵያ ከምግብ ደህንነት ችግር ፈጣሪ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የሚስተዋሉ ችግሮችንም ለመቅረፍ በ24 ከተሞች በተደረገ ቅኝት የሚያስፈልጉ የገንዘብ ድጋፎችን በማድረግ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንኳን ለምግብ ደህንነት ቀን አደረሳችሁ አደረሰን የሚል መልዕክታቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ወ/ሪት ሄራን ገርባ ገልጸው፤ የዚህ ቀን መከበር ዋና አላማ የምግብ ወለድ በሽታዎች ትኩረት እንዲያገኙ ይህንንም ለመከላከል፣ ከተከሰተ ደግሞ በቀላሉ መለየት እንድንችል እንዲሁም የከፋ ችግር ሳይፈጠር መቆጣጠር እንድንችል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለማንቃት እንዲያስችል መሆኑን ጠቅሰው የምግብ ዋስትና ለሰው ጤና፣ለኢኮኖሚ ብልፅግና ፣ለግብርና፣ ለገበያ ተደራሽነት፣ ለቱሪዝም እና ዘለቄታዊ ልማት ትልቅ አስተዋፆኦ ስላለው የምግብ ደህንነት የሁላችንም ሀላፊነት መሆኑን በመገንዘብ እያንዳንዱን ቀን የምግብ ደህንነት ቀን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው ይህ የውይይት መድረክ የተሳካ እንዲሆን ላደረጉ አካላት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንኳን አዳረሳችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም የምግብ ደህንነት ጉዳይ የሁሉ ሰው ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው ምግብ ደህንነቱ የተጠበቀ ከሆነ ለመጪው ትውልድ ትርጉም ያለው በመሆኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስቀረት የቁጥጥር ስራ ላይ መስራት እንዳለበት፣ የቁጥጥር ስራዎች ላይ በግብርና ምርት ላይ እና ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች ላይ ሰፊ ስራ መሰራት ስላለበት አንድ ላይ ተባብረን ተቀናጅተን መስራት እንደሚገባ እንዲሁም፣ ቀድመን ችግሮች ሳይፈጠሩ የምግብ አመራረቶች ፣ አስመጪዎች ላይ ፣ አከፋፋዮች አገር ውስጥ ሲያስገቡና ከገባ በኋላ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ፣ የህግ አካላት ትልቅ ሚና ስላላቸው የቁጥጥር ስራ ላይ አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ ከህብረተስቡ ጋር በጋራ በመሆን መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች አባ ገዳዎች ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብ ተደራሽነት የማድረግ ተግባርን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርበዋል።