በደቡብ ምዕራብ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ያጠናቀቁ ባለሙያዎች ተመረቁ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ከተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ተውጣጥተው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጣና ለ3 ወራት ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የካቲት 10/2015 ዓ.ም በጂማ ከተማ በተዘጋጀው 3ኛው ዙር ስልጠና ላይ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ በሽታዎችና ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየት ለመከላከል እና ለመቆጣጥር የሚያስችል ስልጠና ለጤና ባለሙያዎች በመስጠትና አቅም በመገንባት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነው፡፡
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና መሰረታዊ የኮምፒውተር እወቀት፣ የበሽታ ቅኝት መረጃ አሰባሰብ፣ እና በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት ስራ እንዲሁም ወረርሽኝ በአንድ አካባቢ ሲከሰት ቅድሚያ ሊወሰዱ የሚገባቸው ጉዳዮች፣ ሳይንሳዊ ገለጻ፣ የወረርሽኝ ሪፖርት አቀራረብ፣ መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች፣ የወረርሽኝ መንስኤ እና ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍል የትኛው ነው የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ደግሞ በሁለተኛው ዙር ስልጠና ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን ከስልጠናው አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በስልጠናው የማጠቃለያ ፕሮግራም ወቅት ተገኝተው እንደተናገሩት መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጣና በኢንስቲትዩቱ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ረጅም ጊዜ የሚውስድ መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ ስልጠናውን የወሰዱ ባለሙያዎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ከክልሉ ይህንን እድል አግኝተው ስልጠናውን ያጠናቀቁ ባሉሙያዎች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት መሰረት በማድረግ በቀጣይ በክልላቸው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ታምራት ቦጋለ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በክልሉ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ፣ አበረታች ውጤትም እየተመዘገበ መሆኑንና በቀጣይ ስልጠናውን ያጠናቀቁ ባለሙያዎች የሕብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አንጻር የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ሶስቱንም ዙር የስልጠና ፕሮግራም ተከታትለው ያጠናቀቁ የጤና ባለሙያዎች የተሰጠውን ስልጠና አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የእለት ከእለት የጤና አገልግሎቶች ውጤታማ እና በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ከስልጠናው ከፍተኛ እውቀት እንደጨበጡ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱ ዙር ስልጠና እና በ3ኛው ዙር የመስክ ምዘና ተሳትፈው ያጠናቀቁ አማካይ ውጤታቸው 70 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ 19 የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡