ሶስተኛው ዙር እና የመጨረሻው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከል የቅድመ ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ከተለያዩ ወረዳዎች ተውጣጥተው መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ለ3 ወራት ወስደው ላጠናቀቁ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች የካቲት 3/2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው 3ኛው እና የመጨረሻው ዙር ስልጠና ላይ የእውቅና ሰርተፍኬት ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዋና አላማ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ በሽታዎችና ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየት ለመከላከል እና ለመቆጣጥር የሚያስችል ስልጠና ለጤና ባለሙያዎች በመስጠትና አቅም በመገንባት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ነው፡፡
ስልጠና በሶስት ዙር የተሰጠ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር መሰረታዊ የኮምፒውተር እወቀት፣ የበሽታ ቅኝት መረጃ አሰባሰብን፣የቅኝት ጥቅል ሪፖርት ምን እንደሚመስል እንዲሁም የሚቀርቡ ሪፖርቶች ምሉዕነት፣ወቅታዊነት፣ ማካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች እና በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት ስራ ስርተው ለሁለተኛው ዙር ስልጠና እንዲሳተፍ የሚያስችላቸውን የግንዛቤ ስልጠና መውሰዳቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በሁለተኛው ዙር ስልጠና ደግሞ ገለጻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዴት ይቀርባል፣ ወረርሽኝ በአንድ አካባቢ ቢከሰት በቅድሚያ ምን መደረግ አለበት፣የወረርሽኝ ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በምን መልኩ ይቀርባል፣ምን ምን ጉዳዮች መካተት አለባቸው፣ የወረርሽኙስ መንስኤ ምን ነበር፣ የትኛው የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃ የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን ከስልጠናው አስተባባሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ ከበበው የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አሸናፊ አያሌው እና ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ በAFENET የምስራቅ አፍሪክ ቀንድ ሀገራት ዳይሬክተር በስልጠናው የማጠቃለያ ፕሮግራም ወቅት ተገኝተው የስልጠናውን ጠቀሜታ፣ አሁን ካለው ዓለም አቀፍ በርካታ ወረርሽኝ አንጻር ሰልጣኝ ባለሙያዎች ሊወስዷቸው እና ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ኃላፊነት አስመልክቶ የተለያዩ የምክረ ሐሳብ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከመጀመሪያው ዙር እስከ መጨረሻው ዙር የተሰጠው ስልጠና የጤና ባለሙያዎቹ ለሚሰጡት የእለት ከእለት የጤና አገልግሎቶች ከፍተኛ እውቀት እንደሰጣቸውና በዚህም መሰረት የሕብረተሰቡን ጤንነት ለማስጠበቅ በትጋት እንደሚሰሩ እና ተገቢውን አገልግሎት እንደሚሰጡ ባለሙያዎቹ በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱ ዙር ስልጠና እና በ3ኛው ዙር የመስክ ምዘና ተሳትፈው ያጠናቀቁ አማካይ ውጤታቸው 70 ከመቶ በላይ ያስመዘገቡ 27 የጤና ባለሙያዎች የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡