ቀጣዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባዔ ጅጅጋ እንደሚካሄድ ታወቀ
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በሐዋሳ ከተማ ከነሐሴ 6 – 8/2013 ያዘጋጁት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባኤ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጣዩም ጉባዔ በጅጅጋ ከተማ እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል፡፡
ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ በእንኳን መጣችሁ መልዕክታቸው በዚህ ጉባዔ የተለያዩ ወሳኝ ውይይቶች የሚኖሩ ሲሆን ከነዚህ ውይይቶችም የምንወስዳቸውን ግብዓቶች በመጠቀም ለቀጣይ ስራችን መሳካት የምንጠቀምባቸው ሲሆን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በማመን እንኳን ወደ ሐዋሳ ከተማ በደህና በጣችሁ በማለከት የተሳታፊዎችም ቆይታ ያማረ እና የተሳካ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
በመቀጠልም የጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ በመግቢያ ንግግራቸው የሚከተለውን ብለዋል፣ ‹‹እንደሚታወቀዉ በአለም አቀፍ እዲሁም በአገራችን የጤና ስርአቱን ተፅእኖ እያደረጉ ያሉት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መሆናቸዉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የአለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በተደጋጋሚ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች እንዲሁም በተፈጠሮ እና በሰዉ ሰራሽ የሚከሰቱ ክስተቶች መሆናቸዉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች የአመራር ስራዎችን ለማሳለጥ እና ምላሽ ለመስጠት ያስችል ዘንድ መደበኛ በሆነ መልኩ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ጉባኤ በእየ እሩብ አመቱ እየተከታተል እና እየገመገመ ይገኛል፡፡ በጤና ሚኒሰቴር በሁሉም መዋቅር በአለም አቅፍ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተዉን የኮቪድ ወረርሽኝ ፣የወረርሽን ምላሽ በተቀናጀ መልኩ ለመምራት በማእከል ደረጃ የወረርሽኝ ማእከል ቁጥጥር ማእከል ወደ ስራ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡
ከዚህም ባሸገር በክልል ደረጃ የሚገኙ የማስተባበሪያ ማእከላትን ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ አንጻር የቴክኒክ፣ የግብአት እና የመዋእለ ነዋይ ድጋፍ በማድረግ የራሳቸዉ የሆነ የነጻ የስልክ ጥሪ በማእከል እንዲኖራቸዉ በማስቻል የኮቪድ እና የሌሎች ወረርሽኞችን ጭምጭምታ በመለየት መደበኛ የሆነዉን የበሽታዎች ዳሰሳ እና ቅኝት ከምንግዜዉም በበለጠ መልኩ እንዲጠናከር ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በኮቪድ ምክንያት መደበኛ የጤና አገልግሎቱ መስተጓጎሉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዳሰሳ፣ቅኝት እንዲሁም ምላሽ ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡››
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር በበኩላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥርን በሁሉም መዋቅሮች ለማሳለጥ የሚረዳን መድረክ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ፡፡ በመድረኩ ላይ ከዚህ በፊት የሰራናቸውን ስራዎች የምንገመግምበት፣ ያጋጠሙን ችግሮችን የምንፈትሽበት፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት፣ ባለፈው ጉባዔ ላይ ያስቀመጥናቸውን አቅጣጫዎች ምን ላይ እንደደረሱ፣ አዲስ የተከሰቱ እና በድጋሚ የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ ተወያይተን ቀጣይ መፍትሔዎችን የምናፈላልግበት የውይይት መድረክ እንደመሆኑ መልካም አፈጻጸማችንንም የምንለዋወጥበትም ጭምር ነው፡፡ ይህም ደግሞ ኮቪድ-19ን እና ሌሎች ወረርሽኞችን እንዴት በተሳካ ሁኔታ ምላሽ እንደተሰጠ እና በነበሩ የክትባት ቅስቀሳ ዘመቻዎች የነበሩ ልምዶችን የሚቃኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ጉባዔው በተሳካ መንገድ የተካሄደ ሲሆን በመጨመረሻም የችግኝ ተከላ፣ የመስክ ጉብኝት፣ የማስታዎሻ ሽልማት እና የቀጣይ አስተናጋጅ ሀገር መረጣ ተካሂዶ ለሚቀጥለው ጅጅጋ ከተማ መመረጧ ታውቋል፡፡