በሀራችን የጤና አትላስ ሰነድ ይፋ ሆነ
በሀገራችን የጤና ስርዓት ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ የሆነው የጤና አትላስ የመጀመሪያው ሰነድ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን የጤና አትላስ ( Health Atlas) ለምረቃ በቅቷል፡፡ ይህ የጤና አትላስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 1990-2019 (እ.ኤ.አ.) በተለያዩ ክልሎች እና አካባቢዎች የተከሰቱ በሽታዎች እና የበሽታዎችን ስርጭት ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ አትላስ ዋነኛ ተጠቃሚዎች የጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ሲሆኑ በተለያዩ ውሳኔዎች ወቅት መረጃ እና ምርምርን መሠረት ያደረገ ውሳኔን እንዲወስኑ እገዛ ያደርጋል ተበሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ዶ/ር ሩት ንጋቱ በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ችፍ ኦፍ ስታፍ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት በሀገራችን የጤና ስርዓት ላይ ያለውን የመረጃ አያያዝ አዘምኖ እና አደራጅቶ መረጃን በተሻለ ሁኔታ በመተንተን ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበው የጤና መረጃ በጤናዉ ዘርፍ የሚካሄዱ ምርምሮችን ለማከናወን፣ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት፣ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት እና ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ዓይነተኛውን ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር አሰፋ ደሬሳ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የም/ዋና ዳይሬክተር አማካሪ በበኩላቸው የሀገራችን የጤና ዘርፍ ብዙ ምርምሮች እና ጥናቶች የሚያስፈልጉት መሆኑ በዝርዝር አስረድተው ይህንንም ለማሳካት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጤናዉ ሴክተር የተለያዩ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለጤና ሚኒስቴር የቴክኒክ ክንፍ እንደመሆኑ መጠን ለፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሳይንሳዊ መረጃዎችን በማመንጨት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አወቀ ምስጋናው በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል አማካሪና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን ረዳት ፕሮፌሰር ባቀረቡት ገለጻ ስለ ጤና መረጃ ጠቀሜታ በጥናት የተደገፈ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር አወቀ ጥናቱ ከ800 በላይ ባለሙያዎችን ያሳተፈ እና ላለፉት አምስት አመታት የተካደ እና የሀያ ዘጠኝ አመታት ዳታን የተጠቀመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ጥናቱ በጤናው ዘርፍ ትልቅ እመርታና ለውጥ ለማምጣት ብሎም ያሉ መሠረታዊ ክፍተቶችን ከመፍታቱ ባሻገር የአሠራር ወጥነትን እንደሚያመጣ አስረድተዋል፡፡፡ በእለቱ የተመረቀው ሌላው ጥናት ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያለፈችበትን የጤና ስርዓት በጠንካራ እና ደካማ ጎን ያሳየ ሲሆን ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
ዶ/ር ከድር ሰኢድ በዚሁ መርካሾ ላይ የጤና መረጃ አጠቃቀም እና ማጋራትን ላይ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት በሁለቱም ጽሁፎች ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በዚህ ወርክሾፕ ላይ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ ተመራማሪዎች፣የክልል ጤና ቢሮ ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በመጨረሻም ወርክሾፑ የሚካሄድበት ሳምንት (ከመጋቢት 05 እስከ 09 2014 ዓ. ም.) (March 14-18, 2022 G.C.) የጤናመረጃ ሳምንት (Health Data Week) ተብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እንዲታሰብ ከስምምነት ተደርሷል።