በሀገር አቀፍ ደረጃ ምክንያታዊ የሞት መጠንን ለማወቅ የሚያስችል የቅኝት መመሪያ ተዘጋጀ
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የበሽታዎችና የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ መስጠት ዳይሬክቶሬት ከጤና ጥበቃ እና ከክልል የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በሃገር አቀፍ ደረጃ በበሽታ ምክንያት የሰዎችን ሞት መጠን ለማወቅ የሚያስችል የቅኝት መመሪያ መዘጋጀቱ ግንቦት 11/2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ይፋ አደረገ፡፡
ወ/ሮ ሮዚና ታሪኩ የበሽታዎችና የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ መስጠት ዳይሬክቶሬት የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ዳሰሳ እና ምላሽ መስጠት ቡድን አስተባባሪ የተዘጋጀውን መመሪያ አስመልክቶ እንደተናገሩት የሞት መጠንን ለማወቅ የሚያስችል የቅኝት መመሪያ ለማዘጋጀት እንደመነሻ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መሆኑንና መመርያው በህብረተሰብ ጤና አደጋዎች የሚሞቱ ሰዎችንም ጭምር ማካተት እንዳለበት ስለታመነበት ሁሉን አቀፍ ምክንያታዊ የሞት መጠንን የሚያሳወቅ መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የመመሪያውን አስፈላጊነት ወ/ሮ ሮዚና ሲያብራሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ ወረርሽኞች ሲከሰቱ የሞት መጠንን በትክክል ለማወቅ እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበረው የሞት መጠን ምን ነበር፣ በሽታው በብዛት የሚያጠቃው ህጻናትን ወይስ አዋቂዎችን ነው፣ በተለይ ደግሞ የትኛውን የጾታ ክፍል እያጠቃ ይገኛል፣ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው በገጠር ወይስ በከተማ የሚለውን በትክክል ለማወቅ የሚያስችል መመሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሮዚና አያይዘውም በምን መልኩ መረጃዎች እንደሚሰበሰቡና ከማን እንደሚሰበሰቡ፣ ደረጃቸውን ጠብቀው ለሚመለከታቸው በምን መልኩ እንደሚተላለፉ፣ የሚፈለጉትስ መረጃዎች ምን ምን ጉዳዮችን ማካተት እንዳለባቸው፣ የክትትልና ምዘና ሂደቶች ምን መምሰል እንእንዳለባቸው እና የተሰበሰቡት መረጃዎች ትክክለኝነት በምን እንደሚለኩ፣ የሚሉ ወሳኝ ጉዳዮች በመመሪያው የተካተቱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ ኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር መመሪያው መጠናቀቁን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት የተዘጋጀው መመሪያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጉዳት ሳያደርሱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ ተግባራዊነቱ ላይ በተዋረድ ከባለድርሻ አካላትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደ አንድ የስራ ድርሻ ሆኖ እንዲተገበር አጥብቀን እንሰራለን ካሉ በኃላ በመመሪያ ዝግጅቱ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ ለተወጡ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ፣የሁሉም ክልሎች የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር እና የአጋር ድርጅት ተወካይ ባለሙያዎች በበመሪያ ዝግጅቱ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡