በሃገር አቀፍ ደረጃ ኮሌራን ለማጥፋትና ለመቆጣጠር የእቅድ ረቂቅ ስነድ እየተዘጋጀ ነው
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደ ጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የባክቴሪያል በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከየካቲት 9 እስከ 13/2012 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በኩሪፍቱ ሆቴል በሃገር አቀፍ ድረጃ ኮሌራን ለማጥፋት የሚያስችል የኮሌራ በሽታ ማጥፊና መቆጣጠሪ የእቅድ ረቂቅ ስነድ ለማዘጋጀት አውደ ጥናት እያካሄደ ነው፡፡
የአው ደጥናቱ ዋና አላማ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ መስሪያ ቤቶችና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባባር ኮሌራን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለማጥፋትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ነው፡፡
አቶ መስፍን ወሰን የበሽዎችና የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ ተ/ዳይሬክተር በአውደጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት የሚዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ሀገራችን በ2030 በሃገር አቀፍ ደረጃ ኮሌራን ለማጥፋትና በበሽታው የሚሞቱትን 90 በመቶ ለመቀነስ የተያዘውን ፕሮግራም እና እንቅስቃሴ በተሻለ ደረጃ ጥንካሬ የሚሰጥ መሆኑን እና ለዚህም የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ተግብር ስለሚጠይቅ የረቂቅ ሰነዱ ዝግጅት የተለያዩ ባለድርሻ መስሪያ ቤቶችን ያካተተ አውደ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አግሪ ቢተግሪንዝ የአለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች እና ምላሽ አስተባባሪ ድርጅቱን በመወከል ስለ ረቂቅ ሰነዱ አጠቃለይ ሁኔታ ንግግር ያደረጉ ሲሆን አቶ ሙከሚል ሁሴን የኢንስቲትዩቱ የባክቴሪያል በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ሰጪ ቡድን ሃላፊና የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ በበኩላቸው ኮሌራን ለማጥፋት ከሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የኮሌራ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች የመለየት እና ሌሎችም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ከመግለጻቸውም በላይ የኮሌራ ማጥፊያና መቆጣጠሪ ረቂቅ ሰነድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር አለማቀፍ የኮሌራ ማጥፊና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃል ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ መሰረት አድርጎ የሚዘጋጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ ሰነዱ ከተዘጋጀ በኋላ በድጋሚ በባለድርሻ አካላትና በከፍተኛ ሃላፊዎች ተገምግሞ ለአለም አቀፍ የኮሌራ ማጥፊና መቆጣጠሪ ግብረ ኃይል (Global Task Force on Cholera Control) የሚቀርብ መሆኑን አስተባባሪው አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ ሰነዱን ለማዘጋጀት የሚያገዙ የተለያዩ የቅኝት መረጃ ጽሁፎች አውደ ጥናቱ ላይ የሚቀርቡ ሲሆን የትምህርት፣የግብርና፣የጤና፣የውሃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣የአደጋ መከላከል ኮሚሸን ፣ የሁሉም ክልል የውሃና የጤና ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የተለያዩ አጋር ድርጅት ተወካዮች አውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ ፡፡