በልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ዙሪያ ያተኮረ የምክክርና የንቅናቄ መድረክ ተከናወነ
በሕብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የማሕበረሰብ ተሳትፎ፤ የማህበረሰብ አቀፍና በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት ሥርዓት እንዲሁም በአየር ለውጥ ላይ ተመስርቶ የሚከሰቱ በሽታዎች ቅኝት ሥርዓት ላይ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የሚሰሩ ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ልዩ ልዩ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለው እገዛ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጠ።
አቶ ሻምበል ሀቤቤ በኢትዮጵያ የሕበረስብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያና መረጃ ሥርዓት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የካቲት 16/2015 በተከፈተው የምክክርና የንቅናቄ መድረክ ላይ በመገኘት ባይረጉት ንግግር በሀገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ ያሉትን መደበኛ የጤና ቅኝት ስርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልፀው ከጤና ውጭም ያሉ መረጃዎች በጤናው ሥርዓት ውስጥ ለሚሠሩ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ቅድመ መከላከል ስራዎች ያላቸው አሰዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የወረርሽኝ ምላሽን ውጤታማ የሚያደርገው ጠንካራ የማሕበረሰብ ተሳትፎ ሲኖር በመሆኑ ይህንን በተመለከተም ሊሰራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ሚና በመለየት በቀጣይ ለሚሰሯቸው ስራዎች የጋራ የሆነ መነሻ የስራ መርሀ ግብር ኢንደሚነድፍ የታወቀ ሲሆን በመድረኩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ከፌደራል እና ከክልል የተውጣጡ እንዲሁም የአለም አቀፍ ተቋማት በለድርሻ አካላት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።