በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ማቋቋም

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር አስፈላጊውን የሰው ሃይል፣ ፋይናንስ እና ሌሎች ግብዓቶች አሰባስቦ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ማቋቋም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ተገለፀ።
———————————————————
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያደርግ የነበረውን ሰብዓዊ ድጋፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የስራ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ፡፡
የመድረኩ ዓላማም ድርጅቱ ለድንገተኛ አደጋዎች ሲሰጥ የነበረዉን ሰብዓዊ ምላሽ መገምገም፣ አንገብጋቢ የሆኑ ክፍተቶችና ድክመቶችን መለየት፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመር፣ እና ከነዚህ በመነሳትም ድርጅቱ ለወደፊት በተሻለ መልኩ የድንገተኛ አደጋዎች ሰብዓዊ ምላሽ እና የጤና ስርዓት ማጠናከር እና መልሶ ማገገም ስራዎች ለመስራት የሚያስችል ግንዛቤ ለማግኘት እንደሆነ የድርጅቱ ተወካይ ዶ/ር ፓትሪክ አቦክ ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እንደገለጹት ይህ መድረክ መንግስት፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ በመሆን የተቀናጀና የተናበበ ዕቅድ አዘጋጅተው ሀብት በማሰባሰብ ትርጉም ያለው ሰብዓዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጦርነትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያከናወናቸው የድንገተኛ ህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰብዓዊ ድጋፍ አፈፃፀም ሪፖርት በኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አመራር ሬዚሌንስና ሪከቨሪ ዳይሬክተር በዶ/ር ያረጋል ፉፋ ቀርቦ ሰፋ ያለ ዉይይት የተደረገበት ሲሆን በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል፣ የአፋር ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል፣ የሶማሌ ክልል፣ እና የትግራይ ክልል ከዓለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያከናወኗቸውን የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይቶች ተደርገውባቸዋል፡፡
በስተመጨረሻም በመተባበርና ቅንጅታዊ አሰራር በማስፈን አስፈላጊውን የሰው ሃይል፣ ፋይናንስ እና ሌሎች ግብዓቶች አሰባስቦ በሚፈለገው መጠንና ጥራት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በተለይም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱትን መልሶ ማቋቋም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን መግባባት ተደርሷል፡፡