በትንኝ ንክሻ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን (Arboviral diseases) ለመከላከል የሚያስችል የመመሪያ ዝግጅት አውደጥናት እየተካሄደ ነው
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የበሽታዎች እና የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት በትንኝ ንክሻ ተላላፊ የቫይረስ በሽታዎች ቅኝት እና ምላሽ ሰጪ ቡድን በትንኝ ንክሻ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን (Arboviral diseases) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከህዳር 15 እስከ 19/ 2013 ዓ.ም በደብረ ዘይት ከተማ በቢን ሆቴል የመመሪያ ዝግጅት አውደ ጥናት እያተካሄደ ነው፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ በትንኝ ንክሻ ምክንያት የሚተላላፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የመጀመሪያ የመመሪያ ረቂቅ ዶክመንት ለማዘጋጀት እየተካሄደ ያለ አውደ ጥናት ነው፡፡
ዶ/ር ዮሴፍ አስራት በትንኝ ንክሻ ተላላፊ በሽታዎች እና VHF ቅኝት እና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ- ስርዓት ወቅት እንደገለጹት በትንኝ ንክሻ ምክንያት የሚተላለፉ የቫይረስ በሽታዎች በቁጥር ከ500 በላይ መሆናቸውን እና ከነዚህም ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉት ሰውን እንደሚያጠቁ እነዚህም በሽታዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለበርካታ ጊዜ እየተከሰቱ መሆናቸውን፣እንደ ሃገር የበሽታዎቹ ችግርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በትንኝ ንክሻ ምክንያት የሚተላለፉ ሁሉንም የቫይረስ በሽታዎች ጥናት ለማካሄድ እና የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ መመሪያ ለማዘጋጀት ስለማይቻል እንዲሁም እሰካሁን የተዘጋጀ መመሪያ ስለሌለ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በሚገኙት 6 የቫይረስ በሽታዎች ላይ ብቻ በአውደ ጥናቱ ትኩረት በማድረግ የመጀመሪያ ሪቂቅ መመሪያ ዝግጅት የሚደረግ መሆኑን የቡድን አስተባባሪው አያይዘው ገልጸዋል፡፡
አቶ መላኩ ስዩም በትንኝ ንክሻ ተላላፊ የቫይረስ በሽታዎች ቅኝት እና ምላሽ ሰጪ ቡድን ባለሙያ በበኩላቸው በትንኝ ንክሻ ተላላፊ የቫይረስ በሽታዎች መካከል ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቁ የሚገኙት ደንጊ ትኩሳት፣ቺጉንጉኒያ ትኩሳት ፣ቢጫ ወባ፣ዚካ ቫይረስ ፣ዌስት ናይል ቫይረስ እና ሪፍት ቫሊ ትኩሳት ቫይረስ ሲሆኑ እነዚህን በሽታዎች ህክምናቸው ምን ይመስላል፣እንዴትስ መከላከል ይቻላል፣በነዚህ በሽታዎች ወረርሺኝ ቢከሰት የመከላከል፣ የመቆጣጠር እና ምላሽ የመስጠት ሁኔታ ምን መምሰል አለበት የሚሉትን እየተዘጋጀ ያለው መመሪያ ምልሽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠብቅ ገልጸዋል፡፡
የምስራቁ የሃገራችን ክፍሎች እና ሞቃት ቦታዎች በሽታውን አስተላላፊ ለሆኑት ትንኞች መራቢያነት ምቹ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ በእነዚህ በሽታዎች እየተጎዱ ከመሆናቸውም በላይ የበሽታዎቹ ምልክቶች ከወባና መሰል በሽታዎች ስለሚመሳሰሉ ለይቶ ለማከምና ለመቆጣጠር መመሪያው ተዘጋጅቶ እና በሚገባ ዳብሮ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ ሃገር አቀፋዊ ዶክመንት ሆኖ ለሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በመመሪያነት ሊደርስ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
50 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ማለትም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ከኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ዳይሬክቶሬት እና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡