በትግራይ በጦርነቱ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የአእምሮ ጤና፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ ለመስጠት የአሰልጣኞች ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል
በትግራይ በጦርነቱ ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የአእምሮ ጤና፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ለ100 ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመልሶ ማቋቋም እና ሬዚሌንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ያረጋል ፉፋ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የስልጠናው ዓላማ ማህበረሰባዊ ዕሴቶችን እና ዘመናዊ የስነልቦና ህክምና ዘዴዎችን በመጠቀም የማከም፣ ማህበራዊ ትስስሮችን ወደ ነበረበት የመመለስ፣ እና ከፍተኛ ስነልቦናዊ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ለመተግበር የሚረዳ መሆኑን አብራርተዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ ዶ/ር ደበበ ባሩዳ እንደተናገሩት ሴቶች፣ ህፃናትና አቅመ ደካሞች በጦርነቱ በከፍተኛ ደረጃ ለማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ስለሚዳረጉ ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገቢዉን የድጋፍ አገልግሎቶች ለመስጠት ስልጠናዉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የትግራይ ክልል ማህበራዊና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ኃላፊ ጀኔራል ዘዉዱ ኪሮስ በበኩላቸዉ ጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳቶችን በክልሉ ማህበረሰብ ላይ ማድረሱን በማብራራት፥ የአእምሮ ጤና፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ አገልግሎቶችን በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ለሚገኙ በጦርነቱ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች ለማድረስ እንዲቻል ስልጠናዉን በቀጣይነትም በተከታታይ መስጠት እንደሚያስፈልግ በንግግራቸዉ አመላክተዋል።
ስልጠናዉን ያዘጋጀዉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮ፣ ማህበራዊና መልሶ ማቋቋም ቢሮ እና ከሴቶች ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ነዉ።