በትግራይ ክልል የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዚህ የክትባት ዘመቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት እንደሚከተቡ ይጠበቃል።
የክትባት ዘመቻው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የመቐለ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ኤሊያስ ካህሳይ ለዚህ የቤት ለቤት የክትባት ዘመቻ ዕውን መሆን አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመሰግነው ለዘመቻው መሳካት የክልሉ ማሕብረተሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አስፈላጊውን ትብብር አንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ
ሚኪያስ አላዩ በማስጀመሪያ ስነ ስርዕቱ ላይ እንደገለፁት በሃገራችን በክትባት እጥረት ምክንያት የሚመጣ የፖሊዮ
በሽታ (VDPV) ከ2019 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በመከሰቱ ፖሊዮን ጨርሶ የማጥፋት ጉዟችንን
አስቸጋሪ አድርጎታል።
“በአጠቃላይ ከ 2019 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በሃገራችን 66 የሚሆኑ በክትባት እጥረት ምክንያት የሚመጣ የፖሊዮ በሽታ (VDPV) ታማሚዎች ሪፖርት ተደርገዋል። ለዚህም በተለያዩ ዙሮች የክትባት ዘመቻዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፤ በተለይም በ 2021 እና 2022 እ.ኤ.አ. አዲሱን የፖሊዮ ክትባት (nOPV2) በመጠቀም ያካሄድናቸዉ ሁለት ዙር ሃገር አቀፍ የክትባት ዘመቻዎች በጥሩ ተሞክሮነት የሚጠቀሱ ናቸው። ሆኖም ግን አንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች ትግራይን ጨምሮ በጸጥታ ችግር ምክንያት ዘመቻዎቹ ሳይካሄዱ ቀርተዋል፣” በማለት አቶ ሚኪያስ አብራርተዋል።
እንደሚታወቀዉ የአለም ፖሊዮን ጨርሶ የማጥፋት ንቅናቄ (GPEI) ከተመሰረተበት 1988 እ.ኤ.አ. ጀምሮ እጅግ በጣም ብዙ ለማመን የሚከብዱ ስኬቶችን በማስመዝገብ የፖሊዮ ታማሚዎች ቁጥር በ 99% ቀንሶ በአሁኑ ጊዜ በአለማችን በሁለት ሀገራት (አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን) ላይ ብቻ ይገኛል። ሃገራችን ኢትዮጵያም የአለም ፖሊዮን ጨርሶ የማጥፋት ንቅናቄ (GPEI) ከተቀላቀለችበት 1996 እ.ኤ.አ. ጀምሮ እጅግ ጥሩ የሚባሉ ዉጤቶችን በማስመዝገብ በ2017 እ.ኤ.አ. ፖሊዮ ከኢትዮጵያ መጥፋቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ ለአፍሪካ ሰርተፊኬሽን ኮሚቴ አቅርባ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።
በክትባቱ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የሐይማኖት አባቶች፣ የትግራይ ጤና ቢሮ ሃላፊ፣ የክልሉ የካቢኔ አባላት፣
የሐውልቲ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ፣ የአለም የጤና ድርጅት (WHO) እና ዮኒሴፍ (UNICEF) ተገኝተዋል።