በአዋሳ የተሰጠው የመስክ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ተጠናቀቀ
March 21, 2022
ለሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሞያዎች የተሰጠው መሰረታዊ የመስክ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ከሶስት ዙር ስልጠና በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህም 23 ባለሞያዎች ተመርቀዋል።
በዝግጅቱም ወቅት ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በቦታዉ ላይ የተገኙት የስራ ሃላፊዎች፤ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንዲሁም አቶ ማሙሽ ሁሴን እና አቶ ተስፋ ጺሆን የክልሎቹ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ሀላፊዎች ለተነሱት ጥቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም ሎጅስቲክን የተመለከቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው አግባብ መልስ ተሰጥቶባቸዋል።
አቶ ጃፈር ከዛሊ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነት እና የአቅም ግንባታ ዳሬክቶሬት ባለሞያ እና የስልጠናው አስተባባሪ እንደገለፁት ስልጠናው በሶስት ዙር የተሰጠ ሲሆን ከመሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት የበሽታ ቅኝት መረጃ እንዴት እንደሚሰባሰብ ማካተት ያለበትን እና ለሚመለከተው አካል እንዴት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንደሚቀርብ እንዲሁም ወረርሽኝ ቢከሰት ምን መደረግ አለበት መንስኤውስ ምንድነው የሚለውን በሶስት ዙር ስልጠናው ውስጥ የተካተቱ እንደነበር ጠቅለል አድርገው አስረድተዋል።