በአዳማ ከተማ የተሰጠው የመስክ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ተጠናቀቀ
በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ ለሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሞያዎች የተሰጠው መሰረታዊ የመስክ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ከሶስት ዙር ስልጠና በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህም ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ 37 ባለሞያዎች ተመርቀዋል።
በዝግጅቱም ወቅት ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በቦታዉ ላይ የተገኙ የስራ ሃላፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፡፡
አቶ ብርሃኑ ቀናቴ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሪሰርቸር ዳይሬክተር እንደተናገሩት የትምህርት ዕድልን በተመለከተ ከክልሉ ስፋት አንፃር ሁሉንም ለማደረስ አስቸጋሪ ነዉ፡፡ በመሆኑም የመስክ ኢፒዲሞሎጂ የሰለጠኑ ቅድሚያ እንዲሰጣቸዉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ይሞከራል፣ሎጅስቲክን በተመለከተ እንደ ኮምፒዉተር፣ላፕቶፕ ያሉ ለፊልድ ስራ በጣም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዉ ከዚህ ቀደም ዴስክ ቶፕ ለማሰራጨት የተቻለ መሆኑን ገልፀዉ ነገር ግን ሁሉንም ማዳረስ ባለመቻላችን ለቀጣዩ ግን ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ተነጋግረን ተጨማሪ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነትና አቅም ማጎልበቻ ተ/ ዳይሬክተር ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ እንደተናገሩት ሰልጣኞችን ለምርቃታቹህ ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ንግግራቸዉን የጀመሩ ሲሆን ዳይሬክቶሬታችን ይህንን ስልጠና በኦሮምያ ክልል ከዚህ በፊት ሶስት ጊዜ አሰልጥኖ 140 ሰዎች አስመርቋል አሁን ለ4 ጊዜ 37 ባለሙያዎችን በአጠቃላይ 177 ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን አስታውሰዉ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮችን እና የአፍሪካ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ኔትወርክን አመስግነዉ ወደፊትም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የበለጠ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ አፍሪካ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ኔትዎርክ የአፍሪካ ቀንድ ሪጅናል ዳይሬክተር በሰጡት አስተያየት ላይ እንደተናገሩት ሰልጣኞች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ዋናዉ ቢሮአቸዉ ካምፓላ ላይ መሆኑን ገልፀዉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለዉ ቢሮ ድጋፍ የሚያደርገዉ ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ጅቡቲ እና ሶማሌ ሲሆኑ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት እየሰጠ ያለዉ ስልጠና በጣም ጥሩ መሆኑን ተናግረዉ ለስልጣኞቹም ባስተላለፉት መልዕከት ይህ የመስክ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ምርቃት የመጀመሪያቹህ እንጂ የመጨረሻቹህ አድርጋቹ እንዳታዩት እና ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመግባት ዕድል ሰላላችሁ ከክልላችሁ አልፋቹህ ኢትዮጵያን በአፍሪከ ተወዳዳሪ ለማድረግ እያሰባችሁ እንድትሰሩ ሲሉ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደተናገሩት ኮቪድ -19 በኢትዮጵያ ሆነ በአለም ሲከሰት እንግዳ ስለነበረ ሁላችንም ፈርተን እንደነበር አስታዉሰው ነገር ግን ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ባለሞያዎች መጥራት እንደአስፈለገና ነገም ሌላ በሽታ(ወረርሽኝ) ቢከሰት መመለስ እንዲቻል አሁንም አቅማችን በበለጠ መገንባት እንደሚገባን ተናግረዉ በሀገርም ደረጃ ሆነ በክልላችሁ ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ምስጋና አቀርባለዉ ወደፊትም ተጨማሪ አቅም እንዲፈጠርና የተሻለ ዕዉቀት እንዲያገኙ ድጋፋ እንደሚያደርጉላቸዉ ገልፀዋል፡፡
አቶ ጃፈር ከዛሊ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነት እና የአቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ባለሞያ እና የስልጠናው አስተባባሪ እንደገለፁት ስልጠናው በሶስት ዙር የተሰጠ ሲሆን ከመሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት የበሽታ ቅኝት መረጃ እንዴት እንደሚሰባሰብ ማካተት ያለበትን እና ለሚመለከተው አካል እንዴት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንደሚቀርብ እንዲሁም ወረርሽኝ ቢከሰት ምን መደረግ አለበት መንስኤውስ ምንድነው የሚለውን በሶስት ዙር ስልጠናው ውስጥ የተካተቱ እንደነበር ጠቅለል አድርገው አስረድተዋል።
በስተመጨረሻም ሰልጣኞች የምስክር ወረቀታቸውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ፣ ዶ/ር ታጠቅ ቦጋለ የአፍሪካ ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ኔትዎርክ ሪጅናል ዳሬክተር ፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጅነት አቅም ማጎልበቻ ተ/ ዳሬክተር ወ/ሮ ነኢማ ዘይኑ እና አቶ ብርሃኑ ቀናቴ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሪሰርቸር ዳይሬክተር በተገኙበት የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለዋል፡፡