በአገር አቀፍ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥናት (Service Provision Assessment) (SPA) 2021 ስልጠና መሰጠት ተጀመረ
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የስርዓተ ጤና እና ስነ-ተዋልዶ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት የSPA 2021 የመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ በማኔጅመንት ኢንስትትዩት ለ200 ለሚሆኑ መረጃ ሰብሳቢዎች ለ1 ወር የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
በቦታው የተገኙት የኢንስትትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል መልዕክታቸውን አስቀድመው ከዚህ ቀደም ሊተገበር የነበረው የመረጃ አሰባሰብ በኮቪድ ምክንያት በመራዘሙ በዚህ አመት በተደራጀ መልኩ ከተለያዩ ጤና ተቋማት መረጃዎችን ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል።
የስልጠናውም አላማ በመንግስት እና በግል ሆስፒታሎች እንዲሁም በጤና ጣቢያዎች ታካሚዎች ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ስለመስተናገዳቸው የምናይበት ስራ በመሆኑ መረጃ በሚሰበሰብበት ወቅት ዕርስ በዕርሳችሁ ተከባብራችሁ፣ ተጠባብቃችሁ፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም ራሳችሁን ከኮቪድ በመጠበቅ መስራት አለባችሁ ሲሉ አበክረው ገልፅዋል።
በመጀመሪያ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የኢንስትዩቱ የስርዓተ ጤና እና ስነ-ተዋልዶ ጤና ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ ጌታቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀው የዚህ ጥናት ተሳታፊዎች በጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በተደራጀ መልኩ ስለ መሰጠቱ መረጃ የምትሰበስቡ በመሆኑ የተሰጣችሁን ኃላፊነት በመወጣት ትክክለኛውን መረጃ እንድታመጡ አሳስባለው በማለት መልክዕክታቸውን አስተላልፈዋል።