በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ቫይረስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ላቦራቶሪ አገልግሎት የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የ2017 ዓ.ም የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና የጨቅላ ህጻናት ኤች አይ ቪ ምርመራ (VL/EID) ትግበራ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ከሰኔ 25 እስከ 27/2017 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና የጨቅላ ህጻናት ኤች አይ ቪ የምርመራ አገልግሎት ትግበራ የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመገምገምና በመለየት በቀጣይ በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል እና ውጤታማ ስራዎችን በማስመዝገብ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን በበለጠ በመቆጣጠር የሕብረተሰቡን ጤና ለማረጋገጥ ነው፡፡
አቶ ፍቃዱ ያደታ በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ስራ አስፈጻሚ ኃላፊ የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሰሩ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን የጠቀሱ ሲሆን የቫይራል ሎድ እና ኢ አይ ዲ (EID) ምርመራ ሽፋን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች የተሰሩና ተገቢ የሆኑ ውጤቶች የተመዘበቡ መሆኑን፣ በነበረው የምርመራ አገልግሎት ሽፋን ተግባራት ላይ የተለያዩ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን አስታውሰዋል፡፡ እየተካሄደ የሚገኘው የግምገማ መድረክም የቀጣይ እቅዶችን እና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የኤች አይ ቪ ቫይራል ሎድ ምርመራ ሽፋን ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሃገሪቱ ያሉ ጤና ተቋማት የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እና ጥራት ያለው መሰረታዊ የምርመራ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ኤች አይ ቪን በመከላከልና በመቆጣጠሩ ረገድ እጅግ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን፣ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የመያዝ ምጣኔ እ.ኤ.ኢ በ2010 ከነበረበት የ46 በመቶ እና በቫይረሱ የመሞት ምጣኔ 52 በመቶ እንዲሁም ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወ/ሮ ፌቨን ግርማቸው የኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ አገልግሎት ማስፋፋትት ትስስር ዲቪዥን መሪ ኢንስቲትዩቱ በአገር አቀፍ ደረጀ በ11 ወራት ውስጥ የሰራቸውን የላቦራቶሪ አገልግሎቶች፣ የቫይራል ሎድ የአገልግሎት ሽፋንን፣ በአቅም ግንባታ ዙሪያ አጠቃላይ የተሰሩ ስራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችን እና የነበሩ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ በጽሁፍ አቅረርበዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዘርፉን የተመለከቱ የተለያዩ የጥናታዊ ጽሁፍ ውጤቶች፣ ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች በመድረኩ ቀርበው ግምገማ እየተካሄደ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች፣ የፕሮግራም አስተባባሪዎች፣ የአጋር አካላት ተወካዮች የግምገማ መድረኩን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡