የክልሎችን የጤና ደህንነት አቅም ለማጠናከር የአመራርና የፕሮግራም አስተዳደር ስልጠና ተሰጠ EPHI Conducts PMEP Training to Strengthen Regional Health Security Capacity

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልሎችን የጤና ደህንነት አቅም ለማጠናከር የአራት ቀናት (Program Management for Epidemic Preparedness/PMEP/) ስልጠና አስጀመረ።
ስልጠናው ከዚህ በፊት በክልሎች የተካሄዱ የጤና ደህንነት አቅም ግምገማዎች የለዩትን ዋና ዋና ክፍተቶችና ቅድሚያ የሚሹ ተግባራት ወደ ተጨባጭ የሥራ እቅድ፣ በጀትና አፈጻጸም ለመቀየር የአመራርና የፕሮግራም አስተዳደር አቅምን ለማጎልበት ያለመ ነው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ስልጠናውን በማስጀመር ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጤና ደህንነት ዝግጁነት በብሔራዊ ደረጃ ብቻ የሚገነባ ሳይሆን በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በማኅበረሰብ ደረጃ ባሉ መዋቅሮች የሚጠናከር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የጤና ስጋቶች በአካባቢያዊ ደረጃ በፍጥነት ካልተለዩ፣ ካልተገመገሙና ካልተቆጣጠሩ ወደ አገራዊና ዓለም አቀፍ ችግር ሊያድጉ እንደሚችሉም ዶ/ር መሳይ ገልጸዋል። በመሆኑም በስልጠናው የሚዘጋጁ የክልሎች የጤና ደህንነት የድርጊት ዕቅዶች በጠንካራ አመራር፣ በተገቢ የሀብት ማሰባሰብ፣ በተቀናጀ ትብብርና በተከታታይ ክትትል ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በስልጠናው ላይ የተገኙት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ተወካይ ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፣ ስልጠናው የክልሎችን የወረርሽኝ ዝግጁነትና የምላሽ አቅም በመገንባት በኩል ያለው የማይተካ ሚና አብራርተዋል። የጤና ደህንነትን አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ በብሔራዊና በክልላዊ ደረጃ የሚደረገው የተቀናጀ የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ፍቃዱ፤ WHO በስልጠናው የተለዩትን ክፍተቶች ለመሙላትና አቅምን ለማጎልበት የሚደረጉ ተግባራትን በቴክኒክ፣ በሥልጠና ቁሳቁስና በሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ፣ የአንድ ጤና እና የዓለም ጤና ደንብ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የጤና ደህንነት አቅም የሚለካው በተዘጋጁ ሪፖርቶችና ዕቅዶች ብዛት ሳይሆን፣ እነዚህ ዕቅዶች በክልል ደረጃ በሚያመጡት ተጨባጭ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል። በአራቱ የስልጠና ቀናትም በPMEP የተለዩ ቅድሚያ የሚሹ ተግባራትን ወደ ክልላዊ እቅድ፣ በጀት፣ ተጠያቂነትና የሚለካ ውጤት ለመቀየር የሚያስችሉ የአመራርና የፕሮግራም አስተዳደር ክህሎቶች ላይ ትኩረት መደረጉን ዶ/ር ፈይሳ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የResolve to Save Lives የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ የጤና ስጋቶችን በቅድመ-ማስጠንቀቂያ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ የአመራርና የፕሮግራም አስተዳደር ክህሎትን ማጎልበት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የክልሎችን የጤና ደህንነት አቅም ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማጠናከር ከEPHI እና ከክልል የጤና መዋቅሮች ጋር በትብብር የሚደረገውን ሁለገብ ሥራ፣ ዕቅዶችን ወደ ተግባር በመቀየር ሂደት አስፈላጊውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ተቋማቸው አብሮ ለመስራት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
EPHI Conducts PMEP training to strengthen regional health security capacity
—————————-
The Ethiopian Public Health Institute (EPHI) conducted a four-day Program Management for Epidemic Preparedness (PMEP) training to strengthen regional health security capacity.
The training focused on translating identified health security gaps into practical action plans, budgets, and measurable results.
Participants also strengthened skills in leadership, program management, resource mobilization, and accountability.EPHI, WHO, and Resolve to Save Lives reaffirmed their commitment to supporting regions in implementing the plans and strengthening epidemic preparedness and response.