በኢትዮጵያና በአጎራባች ሀገራት የጤና ስርዓትን ለማጠናከር የሚያግዙ ስምምነቶችን እርዳታዎች ተደረጉ፡፡
የሀገራችንን የጤና ስርዓትን በማጠናከር የሀገር ውስጥና ድንበር ተሻጋሪ የጤና በሽታዎችን ለመከላከል እንዲቻል የበለጠ ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
በዛሬው እለት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአውሮፓ ህብረት ድጋፍና በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስተባባሪነት እንዲሁም በሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ተባባሪነት የኢትዮጵያን አጎራባች ሀገራት የጤና ስርዓትና የኮቪድ-19 ምላሽ ለመደገፍ ለኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በተደረገው ልዩ ልዩ የጤና አምቡላንሶችና ቁሳቁሶች ርክክብ እና የመግባቢያ ሠነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት የተሻለ ጤናን መገንባት የሚቻለው የተሻለ የጤና ሥርዓት ሲገነባ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የምርምር ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ-19ና ሌሎች ድንገተኛ ወርረሽኞች የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል ይቻል ዘንዳ በሀገር ውስጥና በድንበር አካባቢ ልዩ ልዩ ስራዎችን በማከናወን እንዲሁም ተገቢውን የጤና ግንዛቤ በማስጨበጥ ተጋዦች በድንበር አካባቢ የሚገኙ ተመላላሽ የህብረተሰብ ክፍሎች ራስቸውን እና ህብረተሰቡን ከልዩ ልዩ በሽታዎች እንዲጠብቁ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክብርት የጤና ሚኒስትርዋ አያይዘውም በድንበር አካባቢ የሚጋጎዙ የጤና ስርዓት የመጠበቅ ስራዎች ለቀጠናዊ ትስስር እና ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የቴና ምርምር ቅኝትን ከማጠናከር እና ከማጎልበት አካያ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ሊያ አይይዘውም የፋይናንሰ እርዳታ በኢጋድ በኩል ላደረጉት ለአውሮፓ ህብረት እና ልዩ ልዩ ድጋፋቸውን ላደረጉት አጋር አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት በሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት የጤና ስርዓታቸውን ለመደገፍ እና ለማጠናከር ተግቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ህዝቦችን ተጠቃሚነት ትስስርና ትብብርን የሚያጎሉ እርዳታዎችና እገዛዎች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ዘወትር አጋር የሆነውን አውሮፓ ህብረትን አመስግነዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ሮናልድ ኮቤ በከፍተኛ ትኩረት ለሚደረገው የክትባት ፕሮግራም አድናቆታቸውን በመግለጽ ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዩኖፕስ ዳይሬክተር እና በአፍሪካ ህብረት ተጠሪ ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን በበኩላቸው ስምምነቱንና እርዳታውን አመስግነው የወደፊት ትብብሮች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት ለማገዥ እንዲረዳ ሶስት አምፑላንሶችና አንድ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ እንዲሁም ሌሎች የጤና ቁሳቁሶች ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በጁቡቲ መንግስታት መካከል በድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ማዕከል ያደረገ ክትባት ዙርያ በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እና በጁቡቲ የጤና ሚኒስትር እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) መካከል የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ፊርማ ስነስርዓት ተከናውናል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ከጤና ሚኒስቴር፤ ከጎንደር ዮኒቨርሲቲ እና ከጅጅጋ ዮኒቨርሲቲ ጋር በህብረተሰብ የጤና ግንዛቤ ማሻሻያ ስራና ምርምር ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ሥነ-ሥርዓትም የተከናወነ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት የጤና ሚኒስቴር እና በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ስራና ምርምር ላይ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓትና የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆንበት የ1.7 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር በላይ በኢጋድ በኩል ለኢትዮጵያ ተደርጋል፡፡ ይህ በምስራቅ አፍሪካ በየነ-መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስተባባሪነት የሚከናወኑ የጤና እና ጤና ነክ ስራዎች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በማጎልበት በለጋሽ ድርጅቶች ደጋፊነት በድንበርና ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች ቁጥጥር አማካኝነት የጤናውን ዘርፍ ማጠናከር ተቀዳሚ አላማው አድርጎ የተነሳ ዘርፈ ብዙ ምላሽ እንደሚሰጥ ይገመታል፡፡