በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (NCD) ተጋላጭነትን የመቀነስ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኖርዌይ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (NIPH) በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (NCD) ተጋላጭነትን የመቀነስ ግብ አቅዶ የሚሰራ የENABLE ፕሮጀክትን በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ጥር 28/ 2016 ዓ/ም ይፋ አደረገ፡፡
የENABLE ጥምረት ዓላማው ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ አመጋገብን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማበረታታት እንዲሁም ከልጅነት ህይወት ጀምሮ በየአካባቢው ሊኖሩ ከሚችሉ የመርዛማ ነገሮች ተጋላጭነትን ለመከላከል ነው።
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ይፍ በተደረገው መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በንቃት ከተሳተፈባቸው የተለያዩ ዘርፎች መካከል ምግብ እና አመጋገብ አንዱ ቁልፍ ትኩረት በመሆኑ ቅድሚያ በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ እስካሁን በርካታ ጥናቶች ማካሄዱን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የENABLE ጥምረት በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የሚከሰቱ ዋና ዋና የ NCD አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችለውን ፕሮግራም ለመፍጠር እና በጋራ ለመስራት ያለመ ፕሮግራም መሆኑንና ጤናማ የአመጋገብ ልምዶችን በማሳደግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ንፁህ እና ምቹ የከተማ አካባቢ በመፍጠር እንዲሁም የአየር ብክለትን በመቀነስ መሆኑን ተናግረዋል።
በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ልክ የተዘጋጁ መፍትሄዎችን በመጠቀም ENABLE ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በነፍሰ ጡር ሴቶች እና በልጆቻቸው ላይ አዎንታዊ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ከመሆኑም በላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ምርታማነትን እና ደህንነትን በመጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ከነበረው መድረክ መረዳት ተችሏል፡፡
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ENABLE፣ የባህሪ ለውጥ፣ በማምጣት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስጋት ቅነሳ እና የተሻለ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ የሚያሳድረውን ለውጥ በተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ከመስራቱም በላይ ENABLE ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የህክምና አገልግሎት ሰጪዎችን አጠቃላይ የጤና አገልገሎት እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልን በጥራትና ቀጣይነት ባለው መንገድ ክትትል በማድረግ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን ከመድረኩ አስተባባሪዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡