በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው
ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 130 ሰዎች ውስጥ 69 (53%) ሰዎች በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ከነበሩ መንገደኞች ውስጥ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በአየር እና በየብስ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ማንኛውም መንገደኛ ለ 14 ቀናት በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ የሚቆዩና ጊዜያቸውንም ሲያጠናቅቁ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተደረገላቸው እንዲወጡ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ እንዲሁም በክልል ከሚገኙ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች በተገኘው መረጃ መሰረት ከ16,000 በላይ ከውጭ ሀገር ተመላሾች ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡ ሲሆን የ14 ቀን ቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እና የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከኮሮና ቫይረስ ነጻ የሆኑ 5,342 ሰዎች ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደገለጹት የአለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ሀገሮች ማድረግ ስለሚኖርባቸው ጥንቃቄዎች መልክቶችን እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለበሽታው የተጋለጡ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስቀመጥ / አንዱ ሲሆን በሀገራችንም ማንኛውም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ መንገደኛ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲገባ ተወስኖ ከውጭ ሀገር ተመላሾች ወደ ህብረተሰቡ ሳይቀላቀሉ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ቦታዎች እንዲቆዩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ አግዟል ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በሀገራችን ያሉ ማህበራዊ እሴቶች ጠንካራ በመሆናቸው ከመደበኛው ግንኙነት ባለፈ ከውጭ ከሚገቡ ሰዎች ጋር የሚኖረው ንክኪዎች አድማሳቸው ሰፊ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም መንገደኞች በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ መደረጉ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመረዳት በማቆያ ውስጥ በሚሆኑበትም ወቅት ከሌሎች ጋር ባለመገናኘት ራሳቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም ወደ ቤተሰቦቻቸውም ሲቀላቀሉ ለህብረተሰቡ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ቢሆንም ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚተላለፉ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ ከመተግበር መዘናጋት የለበትም፡፡
በተጨማሪም ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተውና አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከል በጥብቅ አሳስበዋል፡፡
በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ለመስጠትና መረጃ ለማግኘት እንዲሁም ከምልክቶቹ አንዱን ቢሰማዎት በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ እንጠይቀለን፡፡
ሚያዝያ 22 ፣ 2012 ዓ.ም