በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ የምርምር ስራ የሚያካሂድ ሀሴት (HaSET) ፕሮግራም የማስጀመሪያና ትውውቅ ስነ ስርዓት ተከናወነ
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ሐርቫርድ (Harvard) ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ሀሴት (HaSET) በተሰኘ ፕሮግራም አማካኝነት በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ ለፖሊስ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ የምርምር ስራዎችን ያከናውናል ፡፡
የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የእናቶችና ሕፃናት ህመምና ሞት ለማቃለል በመንግስት በኩል የሚወሰዱ የጤና ማሻሻያ ፕሮግራሞች ሳይንሳዊና ጥናታዊ የምርምር መረጃዎች ላይ መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑና ችግሮቹን ለመፍታት ተግባራዊ እየተደረጉ በሚገኙ ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ብሎም አዳዲስ የፕሮግራም አቅጣጫዎች ለሚያስፈልጋቸው ችግሮች በጥናት የተደገፉ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎቸን በመንደፍ ለፖሊሲ አውጪዎች ማቅረብ ነው፡፡
የፕሮግራሙን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ በእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ምርምር እያደረጉ የሚገኙ ተቋማት እንዱሁም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች አቅማቸውን የበለጠ በማጎልበት ለችግሮቹ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ የሚያስችል ምርምሮችን ማከናወን ነው፡፡
ይህ ፕሮገራም ከጤና ሚኒስቴርና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባብር በእናቶችና ህጻናት ጤና ትግበራ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን በመለየት የምርምር ስራዎችን ክሚያከናውኑ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡ አምስት ድህረ-ምረቃ (Post-doctoral Fellows ) ከፍተኛ የምርምር ባለሞያዎችን እና እንዲሁም በጤናው ዘርፍ በእናቶችን ሕፃናት ፕሮግራም ላይ አስፈጻሚነት የሚሰሩ አምስት ባለሙያዎች (Implementation Fellows ) ቅድሚያ በሚሰጣቸዉ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲሰሩ ብፕሮግራሙ ታቅፈው ዝግጀት የጀመሩ ሲሆን በሂደትም የምርምር ውጤታቸውን ለፖሊሲ ግብአት እንደሚያውሉት ይጠበቃል ፡፡