በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ የተካሄደው የጥናትና የምርምር ግኝቶች ስርጭት ዓዉደ ጥናት ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤናና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት፥ ከቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ ሀሴት (HASET) በተሰኘ ፕሮግራም ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረውን የጥናትና ምርምር ስራዎች ቁልፍ ግኝት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተገኙበት ጥቅምት15/ 20116/ ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ለባለድርሻ አካላት ይፋ አደረገ፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በዓዉደ ጥናቱ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደገለጹት ጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ህዝብ ጤና እንዲሻሻል ለማድረግ በማስረጃ የተደገፉ ፖሊሲዎችን በመቀየስ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ለዚህም የፖሊሲ ምርምርና ስትራቴጂ አመራር አስፈፃሚ መስሪያ ቤት አቋቁመናል፡፡ በመሆኑም የጤና ሽግግር አጀንዳ ዋና አላማ ጥራት ያለው የጤና መረጃዎችን በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት እና ከፍተኛ የጤና ስርዓት አፈፃፀም ለማሻሻል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክትር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ህዝብ የጤና ፍላጎት ለማሟላት ጥራት ያለው ማስረጃ ያስፈልጋል ይህ ደግሞ በአብዛኛው የሚመነጨው በየጊዜው ከሚከናወነው ክትትልና የቅየሳ ፕሮግራም መረጃ ጋር በተቀመጠው ልማታዊ የጤና ተቋማት ሪፖርት አንዱ ሲሆን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በፖሊሲ ማስረጃ መስኮች ከሚሰሩ የተለያዩ ጤና ተቋማትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እና የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ተወካዮች ፕሮግራሙንና የተካሄዱ ጥናቶችን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በእናቶችና ሕፃናት ጤና ዙሪያ የተገኙ ዋና ዋና የምርምር ግኝቶች በአውደ ጥናቱ ላይ ቀርበው የተለያዩ አስተያየቶች እና ሃሳቦች ተነስቷል፡፡
ፕሮግራሙ የድህረ ዶክትሬት እና የትግበራ ባለሞያዎችን በመመልመል አቅም ለማጎልበት ሲያሰለጥን የነበረ ሲሆን ለነዚህም ባለሞያዎች ስልጠናውን በማጠናቀቃቸው ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚሰሩ የምርምር ተቋማት፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም በዘርፍ የምርምርና ጥናት ስራ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ባለሞያዎች የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡