በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ጤና ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተከናወነ፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስትቲዩት ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ጤና ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አከናወነ፡፡ የተከበሩ ዶ/ር መሰረት ዘላለም በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበው የአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ጤና ጋር እንደሚያያዝ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ጌታቸው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስትቲዩት የሥርዓተ ጤና እና ሥነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክተር በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር አውደ ጥናቱ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በጤናው ሴክተር በተለይ በእናቶችና ህጻናት ጤና ዙርያ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማሳየትና የነበሩ ክፍተቶችን ለመለየት እንዲሁም በቀጣይ በተለይ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችን ለማሳካት መከናወን ባለባቸው ዋና ዋና ክንውኖች ዙርያ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስትቲዩትና የጤና ሚኒስቴር ካውንት ዳውን 2030 ከተባለ በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ከሚሰራ የጥናት ቡድን ጋር በመተባበር በቀጣይ የጥናት ውጤቶችን በመገምገም ግንኝቶችን የማዳበር ስራዎች እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል፡፡