በእናቶች፤ በህጻናት እና በወጣቶች ጤና ላይ የሚደረጉ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ

በጤናው ሴክተር በእናቶች፤ በህጻናት እና በወጣቶች ጤና ዙርያ በተካሄዱት በርካታ ስራዎች የተነሳ ሀገራችን አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በዛሬው እለት በተከፈተው አውደ ጥናት መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በምዕተ አመቱ የልማት ግቦች አራትን እና ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች መርህ በተመለከተ በተሰሩ ስራዎች የተነሳ ሀገራችን የእናቶች እና የህጻናት ሞትን በመቀነስ ሂደት ላይ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቧን አስረድተዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ማስቀጠል ይቻል ዘንድ በዚህ ዙርያ የሚሰሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረውና በተናበበ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
አውደ ጥናቱ በጤናው ሴክተር የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የተገኙ ውጤቶችን በተለይ በእናቶች፤ በህጻናት እና በወጣቶች ጤና ላይ እንዲሁም በሥነ-ምግብ ላይ የተገኙ ውጤቶችን የሚገመግም ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በእናቶች እና በጨቅላ ህጻናት ጤና ላይ ኢትዮጵያ ያሳካችው አስቻይ ወይም ምቹ ሁኔታዎችን እንዲሁም በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በጤና ሚኒስቴር የጤና መረጃ የመተንተን የአቅም ግንባታ ላይ እንደሚያተኩር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አውደ ጥናቱ ከዚህም በተጨማሪ በጤና ዘርፍ ላይ ቀደም ሲል የነበሩ ፖሊሲና እስትራቴጂዎችን ከእናቶች፤ ከህጻናት እና ከወጣቶች ጤና አንጻር ያስገኙትን ውጤቶችና ተግዳሮቶች ላይ ግምገማዎችን በማካሄድ ግብአቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለአስፈጻሚዎች እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና አጋር አካላት ትብብር በተዘጋጀው በዚሁ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በቨርችዋል ከካናዳና ከእንግሊዝ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡