በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎችን አስመልክቶ የምርምር እና ቅኝት ስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት ምክክር በመካሄድ ላይ ነው

የኢንስቲትዩቱ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ምርምር ዲቪዥን በቀጣይ 5 ዓመታት በክትባት መከላከል የሚችሉ በሽታዎች አስመልክቶ ከጥር 28 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የእስትራቴጂ ዝግጅት ምክክር በማካሄድ ላይ ነው፡፡
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎችን በሚፈለገው ደረጃ ለመከላከል ይቻል ዘንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተናበበ እስትራቴጂ እቅድ በማዘጋጀት እና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በቀጣይ አምስት ዓመት ተገቢውን ውጤት ለማስመዝገብ ያለመ ነው፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ኃላፊነቶች መከከል ምርምርና ቅኝትን መሰረት በማድረግ የሕብረተሰቡን ጤና ከአደጋ መከላከል ትልቁ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ኢትዮጵያ ጠንካራ ምርምር እና ውጤታማ የክትባት ፕሮግራሞች ተግባራዊ በማድረግ የማህበረሰቡን ጤና እና ደህንነት ከፍ ከማድረጓም በላይ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ የሚፈጥሩ በተለይም የተላላፊ በሽታዎች ጉዳት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ እድገት አሳይታለች። ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች አሁንም ስጋት የመሆናቸው ጉዳይ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምክክር መድረክ ቁልፍ የምርምር አጀንዳዎችን የመለየት፣ የክትባት ሽፋን ደረጃዎችን እንዲሁም በክትባት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩትን ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎችን በመለየትና በመረዳት መረጃ ላይ የተመሰረቱ ስልቶችን ማዘጋጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በእስትራቴጂ እቅዱ መካተት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ባለን እውቀት ላይ ክፍተቶችን በመለየት እና የክትባት አገልግሎት ጥራትን በማጎልበት በማስረጃ የተደገፈ አጠቃላይ የምርምር ስትራቴጂ መፍጠር፤ ተግባራዊ በሚደረጉ ጥናቶች ውስጥ ማህበረሰቡን ማሳተፍ እጅግ ወሳኝ መሆኑን እና በርካታ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማጤን እንዲሁም የክትባት ሽፋንን ለመከታተል የሚያስችል ጠንካራ የክትትል ዘዴዎችን መዘርጋት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ መልካሙ አያሌው በጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም ዴስክ አስተባባሪ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ በክትባት መከላከል የሚችሉ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች በየጊዜው የሚከሰቱ መሆናቸውን፤ ችግሮችንም ለመቅረፍ ሳይንሳዊ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ትርጉም ያለው ውጤታማ ሥራዎችን ማስመዝገብ ተገቢ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ራጂሃ አቡበከር በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ምርምር ዲቪዥን ኃላፊ በምክክር መድረኩ የሚዘጋጀውን እስትራቴጂክ ረቂቅ እቅድ በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የምርምር አጀንዳ፣ የምርምር መስኮች እንዲሁም የባለድርሻ ትብብርን እና ሌሎችም የክትባት ወሳኝ ጉዳዮችን በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የባለድርሻ አካላት ተወካዮች በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለያዩ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡