በውሃ አቅርቦት፣በሳኒቴሽንና በሃይጅን ዙሪያ ከባለድርሻ አአካላት ጋር አገር አቀፍ የምክክር መድረክ እተካሄደ ነው
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በውሃ አቅርቦት፣በሳኒቴሽንና በሃይጅን ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከጥር 29 እስከ 30/2012 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በቢን ሆቴል አገር አቀፍ የምክክር መድረክ እተካሄደ ነው፡፡
የምክክር መድረኩ ዋና አላማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ስለ ውሃ አቅርቦት፣ሳኒቴሽን እና ሃይጅን ዙሪያ የተካሄደውን የዳሰሳ ጥናት መሰረት በማድረግ ከባለደርሻ አካላት በመመካከር ለችግሮቹ የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ ለመግባት ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡
ወ/ሮ ኢክረም ሬድዋን በጤና ሚኒስቴር የሃይጅንና አካባቢ ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመድረኩ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሃይጂንና አካባቢ ጤና አጠባበቅ ላይ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን፣በርካታ የሰራተኛ ቁጥር የያዙ ኢንቨስትመንቶች በሃገሪቱ መስፋፋታቸውን እና ብዙ ህዝብ የሚገኙባቸው ተቋማት ደግሞ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በሽታዎቹ ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ከውሃ አቅርቦት፣ከሳኒቴሽን እና ከሃይጅን አለመሟላት ጋር የተያያዙ መሆናቸውንና ተቋማቱ እነዚህን ማሟላት እና የአካባቢ ንጽህና ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ስለሚገባ በጋራና በቅንጅት ችግሮቹን ለማስወገድ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
አቶ መስፍን ወሰን የኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችና የጤና ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር የምክክር መድረኩን እና የጥናቱን ዋና አላማ በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን አቶ ይበይን ሙሉ ዓለም የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ባለሙያና የምክክር መድረኩ አስተባባሪ በ19 የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የተደረገውን የዳሰሳ ጥናት በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት አብዛኞቹ ተላላፊ የወረርሽኝ በሽታዎች በርካታ ሰዎችን አያጠቁ የሚገኙት በኢንቨስትመንት ተቋማት መሆኑንና ለዚህም የውሃ አቅርቦት፣የሳኒቴሽን እና የሃይጂን አለመሟላት መሆኑን በጥናቱ ተገልጻል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ኢንቨስትመንቶች የውሃ አቅርቦት፣የሳኒቴሽን እና ሃይጅን አለመሟላት ችግሮች እና የተላላፊ በሽታዎች የመሰራጨት ችግር ለማስወገድ ምን መደረግ እንዳለበት በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የኢንቨስትመንት ሃላፊዎችና ተወካዮች፣የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተወካዮች፣የፌዴራል የተለያዩ ተቋማት፣የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና አጋር ድርጅቶች በአጠቃላይ 102 የተለያዩ ባለሙያዎች በምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡