በደቡብ ኦሞ የኮሌራ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
በደቡብ ኦሞ ዞን በበናምፀይ ወረዳ በብራይሌ ከተማ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በዛሬው ዕለት የጤና ሚኒስቴር ሚንስተር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ፣ የኢትዬጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ የደቡብ አሞ ዞን መስተዳድር አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንዲሁም የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በተገኙበት በይፋ ተጀመረ።
አቶ ንጋቱ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በቦታው የተገኙትን ሁሉ እንኳን ይህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሙሉ የሕብረተሰብ ንቅናቄ የመፍጠርና በአካባቢው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ባለመኖሩ የውሃ ማከሚያ ኬሚካል የማዳረስ ስራ እና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን አሁን ለተጀመረው የክትባት ዘመቻ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል። በስተመጨረሻም ለዚህ የክትባት ዘመቻ እውን መሆን አስተዋዕኦ ያደረጉትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል።
አቶ ማሙሽ በበኩላቸው ክትባቱ በሽታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለው ሲሆን አሁንም ንፁህ የመጠጥ ውሃ አጠቃቀም፣ የግል ንፅህና አጠባበቅ ላይ እና የሽንት ቤት አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ስለተደረገው አጠቃላይ አቀባበል አመስግነው በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ስራዎች በመስራት ላይ ያሉ ሲሆን ከነዚህ ስራዎች ውስጥም ይህንን ወረርሽን መከላከልና መቆጣጠር አንዱ እንደመሆኑ ወረርሽኙንም በተለያዩ ወረዳዎች መቆጣጠር ቢቻልም አሁንም በተወሰኑ ወረዳዎች በመከሰቱ የምላሽ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
የጤና ሚንስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀም የአየር ሁኔታ ለውጥ በሀገራችን፣ በአፍሪካ ብሎም በአለም ደረጃ ለተለያዩ የበሽታ ወረርሽኞች መከሰት ዋናው ምክንያት ሲሆን በቅርቡ በደቡብ ኦሞ የተከሰቱት የድርቅና የጐርፍ አደጋዎች ለዚህ ዋና ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ አደጋዎች ደግሞ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች አጋላጭ እንደመሆናቸው በዚህ ክልል በርከት ያሉ ወረዳዎች በኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በመጠቃታቸው የክትባት ዘመቻ ሊጀመር ችሏል።
እንደ ሚንስትር ዲኤታው ገለፃ ተመሳሳይ የመከላከያ ክትባት በሀገሪቱ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከአንድ አመት በላይ ለሆኑ ዜጎች የማድረስ እቅድ እንደተያዘ ገልፀው ለዚሁም ተግባራዊነት የበኩላቸውን ላበረከቱ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው በተለይም በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመሠራት ላይ ያለዉን አጠቃላይ የጤና አደጋዎች ምላሽ ስራ የሚያበረታታ እንደሆነና ለመስገን እንደሚገባው አብራርተዋል።