በጎንደር የመውጫና መግቢያ ኬላ ያለው የጤና አገልግሎት አስመልክቶ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመግቢያና መውጫ ኬላዎችና ተጓዦች ጤና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በጎንደር ከተማ ያዘጋጀው የመግቢያና መውጫ ኬላዎችና ተጓዦች ጤና አገልግሎት ባለድርሻ አካላት አመታዊ የምክክር መድረክ በተሳካ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በሁመራ ኬላ በኩል ስላለው የገቢ እና ወጪ ተጓዦች የጤና ክትትል ሁኔታም በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡
እንደሚታወቀው በሁመራ በሀራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የገቢ እና ወጪ ተጓዦች ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም የጤና ቁጥጥር ስራው ግን እንደቀጠለ መሆኑ ከቀረበው መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡
አቶ ዩሐንስ ዱጋሳ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመግቢያና መውጫ ኬላዎችና ተጓዦች ጤና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዋና ዋና መግቢያና መውጫ ላይ የሚፈጠረውን ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ከሚሰራው ስራ ባሻገር ሕብረተሰቡንም የስራው አካል ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና በጋራ የሚሰራበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ገጸዋል።
አቶ ታምሩ ታደሰ የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያና የመድረኩ አስተባባሪ በበኩላቸው በኬላዎች የሚደረገውን የጤና ቁጥጥር ለማጠናከር እና ለማሳለጥ፥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመለየት እነዚህንም ለመፍታት የሚያስችሉ መንገዶችን፥ የበጀት አመቱን የ9 ወር አፈጻጸም መገምገምና ቀጣይ አቀጣጫዎችን በጽሁፍ አቅርበዋል።
እንደሚታወቀው ተመሳሳይ የምክክር መድረክ ድሬዳዋ እና ሐዋሳ ከዚህ በፊት የተካሄደ ሲሆን ይህ ሶስተኛው ተመሳሳይ የምክክር መድረክ መሆኑ ይታወቃል።
በመድረኩም የፍደራል ፖሊስ፥ የኢሚግሬሽን ባለስልጣን፥ የጉምሩክ ባለስልጣን፥ የመድሀኒት አቅርቦት ባለስልጣን ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣይም የቡድን ውይይት ከተደረገ በኋላ በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ሁኔታወች የተግባር ዕቅድ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።