በጤናው ዘርፍ የምክክር ጉባኤ ተካሄደ
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንግሊዝ አገር ከሚገኘዉ ከለንደን እስኩል ኦፍ ሃይጅንና ትሮፒካል ሜዲስን ጋር በመተባባር በእናቶች፤ጨቅላ ህጻናት እና ልጆች ጤና ጥናት ላይ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል የአንድ ቀን የምክክር ጉባኤ አካሄደ፡፡
የጉባኤው ዋና ዓላማ፡ የእናቶች ፣ ጨቅላ ህፃናት እና ልጆች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የጋራ የምርምር ስራዎችን ለመገምገም ፣ ለማጠናከርና፣ለማሳደግ እንዲሁም ለወደፊቱ የተጀመረውን የምርምርና የአቅም ግንባታ የትብብር ማዕቀፍ ለማዳበር ነው፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር የጉባኤው ታዳሚዎችን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለጹት የምክክር መድረኩ ኢንስቲትዩቱ ከለንደን እስኩል ኦፍ ሃይጅንና ትሮፒካል ሜዲስን ጋር ያለን ግንኙነት ምን እንደሚመስል የምታይበት ከመሆኑም በላይ በእናቶች፤ጨቅላ ህጻናት እንዲሁም ልጆች ጤና ላይ ጥናትና ምርምር ሲካሄድ ያጋጠሙ ችግሮች ምን እንደነበሩ በመለየት በቀጣይ የሚፈቱበትን የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አበበ በቀለ የኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ጤና እና ስነ-ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በእናቶች፤ጨቅላ ህጻናት እና ልጆች ጤና ላይ የተካሄደውን ጥናት ያቀረቡ ሲሆን ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በእናቶችና በህፃናት ጤና ላይ አመርቂ መሻሻል መታየቱን፣ እ.አ.አ. የ2019 በወጣው የኢትዮጵያ መለስተኛ የስነ-ሕዝብ እና ጤና ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት መሰረት ከ1000 ህጻናት ውስጥ እ.ኤ.አ በ2000 ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ሞት 166* የነበረው እ.ኤ.አ 2019 ወደ 55* ዝቅ ማለቱን፤ እ.ኤ.አ በ2000 የጨቅላ-ህፃናት ሞት መጠን 49* የነበረው እ.ኤ.አ 2019 ወደ 30* ዝቅ ማለቱን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
ጉባኤው የእናቶች እና ህፃናት ጤና በኢትዮጵያ አጠቃላይ የጤና ሽፋንና ጥራት ፤ የጤና መረጃን ለዕቅድ መጠቀም እንዲሁም የጋራ መማማር ለለውጥ በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ምክክር አካሂዷል፡፡
በርከት ያሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ከመሆኑም በላይ ክፍተቶች ተለይተው በቀጣይ በሚከናወኑ ጥናቶችና ፕሮግራሞች የእናቶች ፣ የጨቅላ ህፃናት እና የልጆች ጤና ሊያሻሽሉ የሚችሉ ጥናቶች መሰራት እንዳለባቸው የምክክር ጉባኤው ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
ከ150 የሚበልጡ የጤናው ዘርፉ ተመራማሪዎች፣መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የስራ ኃላፊዎች የፖሊሲ አውጭ አካላት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት; የጤና ምርምር ተቋማት፤ የጤና ሙያ ማህበራትና አጋር ድርጅቶች በምክክር ጉባኤዉ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡