በጤናው ዘርፍ ያለውን የምርምር አቅም ውስንነት መቅረፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው የለንደን ስኩል ኦፍ ሀይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሰን ጋር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ሲያከናውን የነበረው ዳጉ የተሰኘው የጥናትና የስልጠና ፕሮጄክት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ አስታወቀ።
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር የፕሮጄክቱ መጠናቀቅ አስመልክቶ በተዘጋጀው የጥናትና የምርምር ኮንፍረንስ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት የዳጉ ፕሮጀክት ትግበራን በተመለከተ ኢንስቲትዩቱ፣ ከአራት የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ማለትም የጎንደር፤ የጅማ፣ የመቀሌ እና የሐዋሳ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም የለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሲን በጋራ በመሆን ተባብረው ያከናወኑትት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በእዚህም ኢንስቲትዩቱ ከዳጉ ፕሮጀክት በጥናትና ምርምሩ መስክ በተጨማሪ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን ከማፍራት አኳያ ተጠቃሚ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በአራት ብሄራዊ ክልሎች ማለትም በአማራ፡ በኦሮሚያ፡ በደቡብ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 52 ወረዳዎች ላይ የተካሄደው ይህ ፕሮጀክት ዋንኛ ጥናቱን ያደረገው ከአምስት አመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ የሚሰጠውን የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ሽፋንና ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እየተከናወኑ ባሉ ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዳጉ ፕሮጀክት በርካታ የሥራ መስኮችን ያቀፈ ሲሆን ይህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን አቅም ማመጣጠኛ ግምገማ፣ ለፈጻሚ አጋሮች ልኬት፣ ትምህርት እና የምዘና ድጋፎችን፤ እንዲሁም ይበልጥ ጠቃሚ በሆነ ሁኔታ፡ በእነዚህ ሁሉ ውስጥ የታቀፈ፣ የአቅም ግንባታ ክፍልን ፕሮጀክቱ አቅፏል። የእዚህ ዓላማውም የህብረተሰብ ጤና ምዘናዎችን በተመለከተ ኢትዮጵያዊ ልህቀት ለማጎልበት እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ እና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን ጥራት እና አጠቃቀም ለማሻሻል ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የለንደን ስኩል ኦፍ ሀይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲሰን በኩል በጋራ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በሌላም በኩል ይህ ፕሮጀክት የዓለም የጤና ምርምር ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል የራሱን አስተዋጽዋ ያደርጋል ተብል የሚጠበቅ ሲሆን ይህን ለአምስት ዓመት የተተገበረውን ፕሮጀክት በገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በኮንፍረንሱ ላይ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል፡፡