ብሔራዊው የሚጥል ህመም ሳምንት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው፡፡
በሚጥል ህመም የተነሳ ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ዜጎች ከፍተኛ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶችና መገለል እየደረሰባቸው በመሆኑ ማህበረሰቡ፡ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የጋራ ርብርቦሽ በማድረግ የህሙማኑን ህይወት የተሻለ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡
“በጋራ በሚጥል ህመም ላይ ያለውን መገለልና አድሎ እናቁም” በሚል መሪ ቃል ብሔራዊ የሚጥል በሽታ ሳምንት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮትን በመወከል ዶ/ር ቤዛ አዲስ ባደረጉት ንግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው ጥናት እ.ኤ.አ በ2019 ዓመት ብቻ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚጥል በሽታ የተከሰተ ሲሆን በዚሁ አመት በአለም አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የሚጥል በሽታ ታማሚዎች እንደነበሩ ጠቁመው ከእነዚህ መካከል ሁለት ሶስተኛው የሚሆኑት ደግሞ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት የሚኖሩ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ዶ/ር ቤዛ አያይዘውም በሀገራችን ኢትዮጵያ በአመት ሀምሳ ሺህ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚጥል በሽታ እንደሚከሰት ገልጸው እኤአ በ2019 በአጠቃላይ 300 ሺ የሚደርሱ በሚጥል በሽታ የተነሳ የሚችገሩ ዜጎች መኖራቸውን አስረድተዋል:: ከእነዚህም መካከል በኦሮምያ፡ በአማራና በቀድሞው አጠራር የደቡብ ከልል 79% የሚሆኑ በህክምና ሊረዱ የሚገባ እና 80% የሚሆኑ አዳዲስ ህሙማን እንዳሉ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር ባደረገው ጥናት ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ እናት የዕውነቱ የኬር. ኤፕለፕሲ ኢትዮጵያ ዋና ዳሬክተር በበኩላቸው ኬር. ኤፕለፕሲ ኢትዮጵያ የሚጥል ህመም በአገራች እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን አስረድተው ማህበረሰቡ ለህመሙ የተሳሳተ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ እና የሚጥል ህመም ህክምና ተደራሽነቱ አናሳ በመሆኑ እንዲሁም የህመሙን ባህሪ ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር በማቆራኛት እና እንደ እርግማን በመቁጠር በርካቶች የጉዳቱ ሰለባ በመሆናቸው በተጨማሪም በሀገራችን በህመሙ ዙሪያ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ አመለካከቶችና ድርጊቶች ህመሙ ያለባቸው ሰዎች ወደ ህክምና እንዳይሄዱ መገለልና መድሎ እንዲደርስባቸው እና ላልተገባ ስነልቦናዊ ጫና እንዲጋለጡ ማድረጉን ተናግረዋል።
የሚጥል በሽታ ተጠቂዎች ህብረተሰቡ ባለው ግንዛቤ እጥረት ምክንያት ወደ ህክምና እንደማይሄዱና አገልግሎት እንደማያገኙ በዕለቱ በተከናወነው ውይይት ላይ የተገለጠ ሲሆን ህሙማኑ ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸው መገለልና መድሎ፤ እንዲሁም በህመሙ ዙሪያ ያሉ ልማዳዊ አስተሳሰቦች ወደ ተሳሳቱ አመለካከቶችና መሸማቀቅ በማምራት በጊዜ የመታከም እድልን ስለሚያሳጣ የሚጥል ህመም ህክምና የታማሚውን ቤተሰብና የህብረተሰቡን ድጋፍ እንደሚያሻው ተወስቷል፡፡ በመሆኑም በህመሙ ምክንያት የሚከሰተውን የአካል ጉዳትና ህመም መቀነስ የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለህመሙ ያለው የተሳሳተ አመለካከትና ግንዛቤ ሲለወጥ ብሎም ህሙማን በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ምርመራና ህክምና ሲያገኙ እንደሆነ ተገልጻል፡፡
በተጨማሪም በህመሙ የሚስቃዩ ኢትዮጵያውያንን የጤና ሁኔታ እንዲሻሻል የሚጥል ህመምን ማከም የሚችል የባለሞያዎች ቁጥር በጤና ተቋማት ላይ እንዲጨምር ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ ለህመሙኑም የህክምና እድሎችን ማመቻቸት ስለህመሙ በህብረተሰብ ውስጥ ያለው አስተሳሰብና አመለካከት እንዲቀየር ግንዛቤ መድረኮችን መፍጠር እንዲሁም ህመሙ እንዳይከሰት የመከላከል ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጻል።
በመድረኩም ስለበሽታው ሙያዊ ገለጻ የቀረበ ሲሆን የሚጥል በሽታ በአካል ጉዳተኝነት፣ በሴቶች፣ ልጆች እና በአእምሮ ጤንነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡