ተሻሽሎ በወጣው አለም አቀፍ የላቦራቶሪ የጥራት ስታንዳርዶች (ISO 15189፡2022) ላይ ለጤና ላቦራቶሪ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ የሕክምና ላቦራቶሪ ማህበር (African Society for Laboratory Medicine /ASLM) ጋር በመተባበር ባለሙያዎችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ተሻሽሎ በወጣው አለም አቀፍ የላቦራቶሪ የጥራት መስፈርቶች (ISO 15189፡2022 Standards) ላይ ከመጋቢት 2-6, 2016 በአዳማ ከተማ በሀይሌ ሬዞርት በተሳካ ሁኔታ ስልጠና አካሄዷል፡፡ በዚህም ስልጠና ከሁሉም የክልል የህብረተሰብ ጤና ተቋማት/ላቦራቶሪዎች ለተውጣጡ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች እና እዲሁም ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልገሎት ሙያተኛ ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን ይህ አዲሱ የISO 15189፡2022 ስታንዳርድ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በአገር ውስጥ ስልጠናው ሲዘጋጅ የመጀመሪያው ነው፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኘተው መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር ሳሮ አብደላ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት የላቦራቶሪ አክሪዲትሽን ስራዎች የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትኩረት (ፍላግ-ሽፕ) በመሆኑ፣ ለዚህ ትግበራ አስፈገላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ኢንስቲትዩቱ አጠናክሮ እደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን አያይዘውም፣ ይህ ስልጠና የላቦራቶሪ አሰራር ሂደቶች ደረጃውን የጠበቀ እና በሁሉም ክልሎች የጤና አጠባበቅ ምርመራዎችን ጥራት ለማሻሻልና ላቦራቶሪዎች አለም አቅፍ እውቅና እዲያግኙና እዲያስጠብቁ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ ለዚህ ስልጠና መሳካት ትልቁን ድጋፍ ላደረገው የአፍሪካ የሕክምና ላቦራቶሪ ማህበር (African Society for Laboratory Medicine /ASLM) ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አለም አቀፍ የላቦራቶሪ የጥራት ስታንዳርዶች (የISO 15189፡2012 Standards) እውቅና ያገኙ የጤና ላቦራቶሪዎች ወደ አዲሱ እስታንዳርድ ለመዘዋወር የሚያስችል አቅምን ከመገንባት እዲሁም በቂ ዝግጅት እዲያደርጉ ከማስቻል አንጻር ጠቀሜታው የጎላ ሲሆን የላብራቶሪ አገልግሎቶችን ዓለም አቀፍ የጥራት እና የብቃት መስፈርት ጋር በማጣጣም የጤና ላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥን ደረጃ ከፍ ለማድረግና እዲሁም የሕክምና ላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት፤ አስተማማኝነት እና የላቦራቶሪ ምርመራን ውጤታማነት በማሳደግ ደረጃ ይህ ስልጠና ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አቶ ዳንኤል መለሰ የላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የገለጹ ሲሆን፣ በስተመጨረሻም አቶ አዲሱ ከበደ የASLM ፕሮጀክት ማኔጀር፣ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን እና ሌሎች ድጋፎችን ተቋማቸው አጠናክሮ እደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡